መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፣ በአዋጅ በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ግብር በጊዜው የማይፈጽሙ ግብር ከፋዮች ሥራው ላይ እንቅፋት እየፈጠረበት መሆኑን ለአሐዱ አስታውቋል።

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ፤ "ቢሮው በዚህ ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን 256 ቢልዮን ብር ለማሳካት እየሰራ መሆኑን አስታሰው፤ በአንዳንድ ግብር ከፋዮች ቸልተኝነት እና ሕግን አለማክበር ምክንያት ተቋሙ ሥራውን በአግባቡ ለመስራት ተቸግሯል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን ወቅቱን ጠብቀው አለመፈጸማቸው፤ ለብልሹ አሰራር በር ይከፍታል" ያሉት ኃላፊው የደረጃ ሐ እና ለ ግብር ከፋዮች እስከ ነሐሌ 30 ቀን 2017 ድረስ የግብር ክፍያቸውን ማጠናቀቅ ቢኖርባቸውም ጥቂት የማይባሉ ግብር ከፋዮች ጊዜው ካለፈ በኋላም ክፍያ እንዳልፈጸሙ አብራርተዋል፡፡

እስከከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ድረስ የግብር ግዴታቸውን መወጣት የሚገባቸው የደረጃ ሀሌታው ሀ ግብር ከፋዮችም፤ የክፍያውን የመጨረሻ ቀናት ሳይጠብቁ በመክፈል ራሳቸውን ከግር ግር እና ከቅጣት ክፍያ እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በአጠቃላይ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ክፍያቸውን ያላጠናቀቁ ግብር ከፋዮች፤ ወደ ቅጣትና ወለድ ክፍያ ከማምራቱ በፊት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ