መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በ"ትምህርት ለትውልድ" ፕሮጀክት በተሰበሰበ ከ85 ቢሊዮን በላይ ብር፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በመላው ኢትዮጵያ መገንባታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፤ "በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በተካሄደው ቅስቀሳ ከሕብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሁሉም ክልሎች ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ ድረስ የሚያስተምሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በተጨማሪም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የማንበብና የመጻፍ መሠረታዊ ክህሎታቸው እንዲዳብር በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል።
"የሕጻናትን የንባብና የጽሑፍ ችሎታ ከመሠረቱ ለማጎልበት ያለመ በፕሮግራም የሚመራ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሠራበት ይገኛል" ሲሉም ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም፣ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ትኩረት ያልተሰጣቸው በመካከለኛ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ "የንባብ ቴክኒክ" በሚል ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው ከክልሎች ጋር እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል የሕዝብ ንቅናቄ በ2015 ዓ.ም. ክረምት ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ መሰረት በቀጣይ አምስት ዓመታት ከ50 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች እድሳት ለማድረግ እቅድ መያዙን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በ"ትምህርት ለትውልድ" ፕሮጀክት ከ85 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው ተገለጸ
