መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የ2017 በጀት ዓመት የ13 ግብር ከፋዮች መዝገብ በማዘጋጀት ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመንግስትን ጥቅም ለማሳጣት የሚያስችል ግድፈት ፈፅመው የተገኙ 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሙያ ፈቃድ እንዲሰረዝ ጥያቄ ማቅረቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ የቅድመ ኦዲት ተግባር በማከናወን የመንግሥትን ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ ለመጉዳት የሚያስችል የገቢ ልዩነት የተገኘባቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ነው ጥያቄ ያቀረበው፡፡
ቢሮው ይኸን ጥያቄውን ያቀረበው በታክስ አስተደደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 48 ንዑስ አንቀፅ 2(ሀ) መሰረት በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ የሂሳብና ኦዲት ቦርድ መሆኑም ታውቋል፡፡

በቢሮው የሙያ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ጥያቄ የቀረበባቸው 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች በቦርዱ የሙያ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆናቸውንም አሳውቋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ቢሮው ከሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሂሳብ መዝገብ አዘገጃጀት ላይ በሚስተዋሉ ግድፈቶች ላይ ከቦርዱና ከሙያ ማህበራት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ማካሄዱን ገልጿል፡፡
በተጨሪም የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ለቢሮው የሚያዘጋጁት የሂሳብ መዝገብ ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች በተመለከተ በመፅሔት በማዘጋጀት ለሁሉም አካል እንዲሰራጭ ማድረጉን ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ቢሮው የሙያ ፈቃዳቻው እንዲሰረዝ ጥያቄ ያቀረበባቸው የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች በ2017 በጀት ዓመት ለግብር ከፋዮች ሂሳብ መዝገብ አዘጋጅተው በቅድመ ኦዲት ከፍተኛ ግድፈት የተገኘባቸውና በታክስ ስወራ የመንግሥትን ጥቅም ሊያሳጡ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ቢሮው የሙያ ፈቃድ ስረዛ በተጠየቀባቸው የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ የሂሳብ መዝገቦችን የማይቀበል መሆኑንም ለግብር ከፋዮች አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ግብር ከፋዩ የሥም ዝርዝራቸውን ከቦርዱ በመጠየቅ የሙያ ሥነ ምግባሩን ጠብቀው በሚሰሩ የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሂሳብ መዝገቡን በማሰራት እንዲያቀርብ አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ