መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ ከምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዊ ቡድን ኢኮዋስን በይፋ ለቀው በመውጣት "የሳህል ግዛቶች ሕብረት" የተሰኘ የየራሳቸው ቡድን የመሠረቱት ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC)ን “የቅኝ ግዛት ጭቆና መሣሪያ” ሲሉ በመጥራት ከፍርድ ቤቱ በይፋ መውጣታቸውን ትናንት ሰኞ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር እ.ኤ.አ. በ2020 እና 2023 መካከል በተደረጉ መፈንቅለ መንግሥቶች በወታደራዊ መሪዎች ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ራሳቸውን ከምዕራባዊያን ለማግለል በማሰብ በቅርቡ የሳህል መንግሥታት ሕብረት (ኤ.ኢ.ኤስ) በተባለ ኮንፌዴሬሽን መስርተዋል፡፡

በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የሚገኙት ሦስቱ ሀገራት ከምዕራቡ ዓለም እየተነጠሉ እንደ ሩሲያ ካሉ ሀገራት ጋር እየተቀራረቡ መምጣታቸውም ይታወቃል።

የሀገራቱ ወታደራዊ መሪዎች በትናንትናው ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፤ መቀመጫውን በኔዘርላንድስ ሄግ ያደረገው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት "በኢምፔሪያሊዝም እጅ ውስጥ ያለ የኒዮ-ቅኝ አገዛዝ ጭቆና መሳሪያ ነው" ሲሉ ከሰውታል፡፡

Post image

"ፍርድ ቤቱ የተረጋገጡ የጦር ወንጀሎችን በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን እና የጥቃት ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ለፍርድ ለማቅረብ እንደማይችል አረጋግጠናል" ብለዋል በመግለጫቸው።

ሦስቱ ሀገራት "ሰላምና ፍትሕን የሚያጠናክሩ አገር በቀል ዘዴዎችን" መፍጠር እንደሚፈልጉም መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ይህም የሀገራቱ ከፍርድ ቤቱ የመውጣት ጥያቄ በይፋ ተግባራዊ የሚሆነው፤ ጉዳዩ በይፋ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከቀረበ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።

ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር በተለይ እንደ ሩሲያ ካሉ ሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እ.ኤ.አ ከመጋቢት ወር 2023 ጀምሮ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ እንደወጣባቸው ይታወቃል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2002 የተመሠረተው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ ሀገራት እንደ ጦር ወንጀሎች ያሉ ከባድ ወንጀል ፈፃሚዎችን ራሳቸው በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፍላጎት እና አቅም በሚያጡበት ወቅት ለፍርድ የማቅረብ ተልዕኮን የያዘ ቢሆንም፤ በዓለም አቀፍ የዳኝነት ስርዓቱ ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡

ከዚህ ቀደም ሃንጋሪ ከ23 ዓመታት አባልነት በኋላ ከዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ