መስከረም 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአዲስ አበባ ከተማ 70 በመቶ የሚሆነውን የወተት ምርት በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች በየሰፍሩ በር እያንኳኩ በጄሪካን የሚሸጡት በመሆኑ፤ ከፍተኛ የሆነ ዘርፈ ብዙ ስጋት ፍጥሮብኛል ሲል የኢትዮጵያ ወተት ዘርፍ ማህበር ለአሐዱ አስታውቋል።

የማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ ይመር በአዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ 70 በመቶ የሚሆነው መደበኛ ያልሆነ የጥሬ የወተት ወይም ሳይቀነባር በዘፍቀደ የሚሸጥ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ወተቱን ከየት እንደሚያመጡት አለማወቅ ብቻ ሳይሆን አደገኛ የሆነ ባእድ ነገር እንደሚቀላቀልበት የገለጹም ሲሆን፤ ይህም መደበኛ የወተት ንግዱ ላይ ኪሳራ ከማድረሱ ባሻገር በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

አሐዱም ስለ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን እንዲሁም፤ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣንን ወተት በየአካባቢው እያዞሩ በሚሸጡ ነጋዴች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥርና ክትትል በተመለከተ ጠይቋል። ‎

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ፍቃድ የሚሰጠው የንግድ ምዝገባ ከተደረገ በኋላ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ማንኛውንም የንግድ ፍቃድ ያወጣ ነጋዴ አድራሻውን ማወቅና መቆጣጠር እንደሚቻል በመግለጽ፤ ነገር ግን በየሰፈሩ እየዞሩ የሚነግዱትን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡

‎ንግድ ቢሮው "ጉዳዩ በዋናነት የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ይመለከተዋል" ባለው መሠረት፤ አሐዱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ጠይቋል

ባለስልጣኑም ወተትን በየሰፈሩ እያዞሩ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ የተደረገ ቁጥጥር አለመኖሩን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር እስጢፋኖስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በየሰፈሩ እያዞሩ ወተትን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሸጡ ነጋዴዎችን የመቆጣጠር ሚና የባለስልጣኑ ባይሆነም በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

አክለውም የወተት ምርት ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በየሰፈሩ እየዞሩ መሸጥ ፈፅሞ የተከለከለ ነው በማለት ገልጸዋል።

‎የወተት ምርት እና የወተት ተዋፅኦ በከፍተኛ ደረጃ ባዕድ ነገር ከሚቀላቀልባቸው ምርቶች መካከል ቀዳሚዎቹ በመሆናቸው፤ በተለይ በየሰፈሩ እያዞሩ በጄሪካን የሚሸጡ ምርቶች ላይ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተጠቁሟል።

ወተትን በጀሪካን እያዞሩ የሚሸጡ ግለሰቦች ብዙ እንደመሆናቸው ማህበሩ በገለጸው ስጋት ምክንያት፤ ተቆጣጣሪ አካል ሊኖረው እንደሚገባ መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ