ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከስራ እና ክህሎት ሚንስትር ጋር በመተባበር ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ዓላማ ሥራቸውን አቋርጠው ቤት የዋሉ የመንግስት ሠራተኛ እናቶችን የሚያበረታታ አሰራር ይፉ መደረጉን አስታውቀዋል።

አዲሱ አሰራር በወሊድ ምክንያት ሥራ ያቋረጡ እናቶች አቅራቢያቸው የሚገኙ ሕጻናትን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ሥራ ላይ ከተሰማሩ፤ እስከ ሦስት ዓመት የሚቆይ ከግብር ነጻ የንግድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚፈቅድ ነው ተብሏል።

ዓላማውም የተሻለ የሕጻናት ማቆያ መፍጠር እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ደረሰ የዚህ አሠራር "ዋነኛ ዓላማው የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና የተሻለ የሕጻናት ማቆያ ማዕከላትን መፍጠር ነው" ብለዋል።

ዳይሬክተሯ በተጨማሪም፤ "ቢሮው መስፈርቶችን ያሟሉ እናቶችን ስልጠና ሰጥቶ ጥራቱን የጠበቀ የሕጻናት ማቆያ ማዕከል መመስረት የሚችሉበትን እድል ያመቻቻል። በተለይም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሩ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በመንግሥት ሕንጻዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ይህ አሠራር፤ የልጆችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ እና ሕጻናቱ ከአካባቢያቸው ሳይርቁ እንክብካቤ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሯ የአዲሱን አሰራር ጠቀሜታ ባብራሩበት ንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ከ872 በላይ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ሲኖሩ፤ በማዕከላቱ ውስጥ ከ13 ሺህ 644 በላይ ሕፃናት እንክብካቤ ጥበቃ እና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።

ዳይሬክተሯ አክለውም ለሕጻናት ማቆያ እንዲሆኑ የሚቋቋሙ ማዕከላት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ቢሮው የክትትል እና ቁጥጥር ሥራን ጨምሮ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ደረጃ እንዲያሟሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖሪያ ቤቶች እና በመንግሥት ሕንፃዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ቢገለጽም ስራ ላይ የሚውልበት ትክክለኛ ጊዜ አልተገለጸም።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ