ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰሜናዊ ጣሊያን ከሚገኘው የቤርጋሞ ኦሪዮ አል ሴሪዮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ላይ በሚገኝ አውሮፕላን ሞተር ተስቦ የገባ አንድ የ35 ዓመት ወጣት ሕይወቱ ማለፉን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኤርባስ ኤ319-111 አውሮፕላን ትናንት ሰኔ 30 ቀን 2017 ጥዋት ላይ ወደ ሰሜናዊ ስፔን አስቱሪያስ ከተማ ለማቅናት ከሚላን ቤርጋሞ አውሮፕላን ማረፊያ ለመነሳት በዝግጅት ላይ እያለ ግለሰቡ አስፋልት ላይ ሮጦ ወደ ሞተሩ መግባቱን ነው መገናኛ ብዙኃኑ የዘገቡት።

Post image

ይህንንም ተከትሎ በአየር ትራንስፖርቱ ላይ በተፈጠረ ችግር ሳቢያ ሁሉንም በረራዎች ለጊዜው መታገዳቸውን አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ይህም ክስተት በጣሊያን ሦስተኛውና በጣም መንገደኛ በሚበዛበት ሚላን ቤርጋሞ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የበረራ ሥራዎች ወዲያውኑ እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል የተባለ ሲሆን፤ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በተደረገ ማሻሻያ አየር መንገዱ ሥራውን መቀጠሉም ተገልጿል፡፡

Post image

ሕይወቱ ያለፈው ግለሰብ ተሳፋሪም ሆነ የአየር መንገዱ ሰራተኛ አለመሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ ግለሰቡ ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ማኮብኮቢያው እንዴት መድረስ እንደቻለ ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል።

የሚላኑ ቤርጋሞ ኦሪዮ አል ሴሪዮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ2024 ብቻ ከ17 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማስተናገዱ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ