ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎ሕብረተሰቡ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያደረገው ደንብ ፀድቆ ተግባራዊ ቢሆንም፤ ፖሊሲ እንደሚያስፈልገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ አደራጎት ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።

በማስተባበሪያ ኮሚሽኑ የበጎ ፍቃድ ግንዛቤ ማስረፅ ቡድን መሪ ቢኒያም ግቻ፤ በተቋማት ላይ የደንቡ ተግባራዊ መሆን ብቻ በቂ ባለመሆኑ የፖሊሲ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

‎የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ተቋማዊ አሰራር ከመዘርጋት አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውንም ቡድን መሪው ገልጸዋል።

‎በደንቡ መሰረት ማንኛውም ሰው አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፤ ባገለገሉበት የሙያ ዘርፍ የምስክር ወረቀት የማገኘት መብት፣ በከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ውስጥ አገልግሎትና የሥራ ዕድል ቅድሚያ እንዲያገኙ የማድረግ መብት እንዳላቸው በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።

‎"በጎ ፍቃደኞች በሚሰጧቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት የማያደረሱ እና የተሰማሩባቸውን ተቋማትና አካባቢ የአሰራር ስርዓት፣ ባህልና እሴት የማክበር ግደታ እንዳለባቸው ተደንግጓል" ብለዋል።

‎በዚህም ለ2017 ዓ.ም ለክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች በተደጋጋሚ እንደሚሳተፉ በኮሚሽኑ የበጎ ፍቃድ ግንዛቤ ማስረፅ ቡድን መሪው ተናግረዋል።

‎በዚህ አገልግሎት ከ800 ሺሕ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥት ሊያወጣ የነበረውን ወጪን ማዳን ተችሏል ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ