ጥቅምት 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የሆነውን ገቢ ማግኘቷ የተገለጸ ሲሆን፤ በአንፃሩ በሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚሸጠው ቡና ዋጋ መወደድ ሲነሳ ቆይቷል።
በዚህም ወደ ውጭ ሀገራት የተላከው የቡና ምርት መጨመር ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንዲቀንስ ማድረጉ ተገልጿል።
በሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት እና አቅርቦት ለማመጣጠን ከተፈለገ መሰራት ያለበት የቡና ምርት መጠንን ማሳደግ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጿል።
የማህበሩ ዋና ፕሬዝዳንት አቶ ግዛት ወርቁ "የሀገር ውስጥ ገበያውን እየረበሸ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ቡናን ከሚያመርት አካባቢ ቡናን ወደ የማያመርት አካባቢ የሚደረገው ዝውውር የምርት አቅርቦቱ ላይ እጥረት እና የዋጋ ውድነት እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህ ችግር ለመፍታትም ቡና የሚጠጣባቸው አካባቢዎች ላይ ቡናን ማምረት እንደሚቻል ገልጸው፤ ነገር ግን የክልል ግብርና ቢሮዎች በትኩረት እየሰሩበት አለመሆኑን አንስተዋል።
ቡና በብዛት በማይመረትባቸው ክልሎች ከሌሎች አካባቢዎች ቡናን ከሚወስዱ፤ የግብርና ቢሮዎች ቡናን ማልማት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ፕሮግራም ሥር የቡና ችግኞች በመስጠት ቡናን ማልማት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በመንግሥት በኩል አምራችነትን የሚጨምሩ ማበረታቻዎችን ማድረግ እና ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እንደ ማህበረሰብ "ቦታ ያላቸው ሰዎች በጓሯቸው ቡናን መትከል ማልማት ይችላሉ" የሚል፤ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
'የቡና ዋጋ ተወደደ' ተብሎ ከሚነሳው ባሻገር ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የቡናን ምርት በከተማም ሆነ በተለምዶ ቡና አብቃይ አይደሉም በሚባሉ አካባቢዎች ማምረት መጀመር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የአንደኛው ሩብ ዓመት የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከታቀደው በታች መሆኑ የግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ 152 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 622 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተላከው ቡና መጠን 114 ሺሕ ቶን ብቻ በመሆኑ፣ ከመጠን አንፃር 38 ሺሕ ቶን ያህል ቡና ሳያሳካ ቀርቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሀገር ውስጥ ያለውን የቡና ፍላጎት ለማሟላት ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛው መፍትሔ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ገለጸ