መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ በሀገር ውስጥ ግንባታው ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ውጤታማና ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋራጮች እና አማካሪዎች እንዲሁ፤ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ባለቤቶችን ለመለየት የሚያስችል ምዘና እና ደረጃ እንደሚወጣላቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤ "የግንባታው ኢንደስትሪዎች ለዘርፉ እድገት የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ግልፅ የሆነ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የተገኘው ውጤትም ለሕዝብ ግልፅ እንደሚደረግ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በሂደቱ ውጤታማ ሆነው የተገኙት እውቅና እንደሚሰጣቸው እንዲሁም በጨረታ ወቅት ደግሞ የተለየ ዕድል የሚያገኙበት የአሰራር ስርዓት እንደሚኖር አስታውቀዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥም ቢያንስ ወደ 20 የሚጠጉ ውጤታማ ተቋራጮች እና አማካሪዎች በየዓመቱ የሚያደርገውን ግምገማና የደረጃ ልየታ በመጠቀም በውጪ ገበያ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአጠቃላይ በግንባታው ዘርፉ ላይ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች የሚለይ እና አሰራሩን የሚያቀላጥፍ ማዕቀፍ ያለው አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የግንባታው ኢንደስትሪው ላይ የሚደረጉ ጥረቶች በተበታተነ መልኩ የነበረ እና በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት የቻሉትንም ሆነ ያልቻሉትን በጥቅሉ የሚያወግዝ እንደነበረ ሚኒስትሯ አንስተዋል።
በመሆኑም "እነዚህ ሥራዎች በፖሊሲ እንዲደገፉና ሕጋዊ ማዕቀፍ ኑሯቸው አፈፃፀማቸው ወጥ እንዲሆን ለማድረግ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምዘናና ደረጃው በመንግሥት ፀድቆ በሥራ ላይ ይውላል" ብለዋል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልነበረ የግንባታው ኢንደስትሪ አዋጅ በሥራ ላይ ከሚገኘው የሕንጻ አዋጅ ጋር ተቀናጅቶ ኢንደስትሪውንና የዘርፉን ሥራዎች ዘመኑን በዋጀ አግባብ በማካተት መዘጋጀቱንም ለአሐዱ አስታውቀዋል።
"አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ከፀደቀ በኋላም በሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል" ብለዋል።
የግንባታው ኢንደስትሪ በሀገርም ሆነ በውጪ የሚመረቱ ግብአቶችን የሚጠቀም፣ ከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የሚያስፈልገው፣ የሰለጠነ በርካታ ባለሙያ የሚያሳትፍና ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፤ ከመንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተከታታይ ሥራዎች እንደሚሰሩ አንስተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ