መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መመረቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይም በዓመት 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ማስጀመራቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

ይህም ፕሮጀክት ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት ባሻገር፤ በኃይል ማመንጫ ዘርፉም 1000 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
"ከሁሉም በላይ ፕሮጄክቱ የጋዝ ማምረቻ ብቻ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት በማቅረብ ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረታችን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለኃይል ማመንጫ እና የክሪፕቶ-ማይኒንግ ሥራዎቻችን አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

በዛሬው በሶማሌ ክልል የተጀመሩት ከተያያዠ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጋር በአጠቃላይ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በተገቢ ክትትል እስከ መጠናቀቂያቸው እንደሚደርሱም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ