መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል ለሚገነቡት የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እንዲሁም የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ. ም. የሁለቱ ፋብሪካዎች ግንባታ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

በመልዕክታቸውም፤ "ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያኮራ ታሪካዊ ሁነት ተፈፅሟል። የሁለት አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል" ብለዋል፡፡

Post image

አክለውም፤ "የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚያስገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ሲጠናቀቅ፤ ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣትና 108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ ያቀርባል" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ በሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ "ሂላል" በተባለ የነዳጅ ስፍራ፤ ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣት፣ የማጣራትና የማጠራቀም ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካው፤ በዓመት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን" ነዳጅ አምርቶ የማቅረብ አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

Post image


"እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪ እድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው። እድሎቻችንን የመጠቀም፣ ትብብሮችን የማጠናከርና ሰላምን የማጽናት የጋራ ኃላፊነታችንን የሚያሳዩ ናቸው" ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ ለእድገት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ነሐሴ 22 ቀን 2018 መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

የማዳበሪያ ፋብሪካ በ40 ወራት እንደሚጠናቀቅ የተገለጸም ሲሆን፤ በግንባታው ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የ40 በመቶ ድርሻ ሲኖረዉ፤ ዳንጎቴ 60 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ