መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ወጥ የሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

ተሽከርካሪዎች ከአንዱ ክልል ወደሌላኛው ክልል ሲንቀሳቀሱ የተለያየ ታሪፍ እንደሚጠቀሙ በሚኒሰቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ ለአሐዱ ተናግረዋል።

Post image

በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ እንኳን የነበረው ታሪፍ ተመሳሳይ እንዳልነበረ የገለጹም ሲሆን፤ ለአብነትም ከመገናኛ ወደ ጣፎ ሲሄድና ከጣፎ ወደ መገናኛ ሲመጣ ይለያይ እንደነበር አንስተዋል።

የታሪፍ ወጥነት አለመኖር የአስተዳደር ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን ያስከትል እንደነበር የተናገሩት አማካሪው፤ በመላ ሀገሪቱ ወጥ የሆነ ታሪፍ እንዲኖር ለማድረግ ሲሰራበት መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከክልሎች ጋር ውይይት በማድረግ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

አጠቃላይ ታሪፉ ከነዳጅ በተጨማሪ የተሽከርካሪው ደህንነት፣ የሹፌርና የረዳት ደመወዝ እንዲሁም፤ የገበያ ሁኔታውን በተመለከተ ጥናት እንደተካሄደበት የገለጹም ሲሆን፤ ታሪፍ የሚወጣው ይህ ሁሉ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው ብለዋል።

በዚህም መሠረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

አማካሪው አክለውም የታሪፍ ክፍያው በተለይም በበዓላት ወቅት እንደሚጨምሩ አንስተው፤ በቀጣይ የሚከበሩ የመስቀል እና ኢሬቻ በአላትን አስመልክቶ ከተቀመጠው በላይ የታሪፍ ክፍያ እንዳይኖር ለማድረግ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ