ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በድሬደዋ፣ በሶማሌ ክልል እና በምስራቅ ሐረርጌ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ምሽግ በማድረግ ከመስከረም 19 ጀምሮ ተሸሽጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ በተወሰደ እርምጃ፤ 43 የቡድኑ አባላት መገደላቸውን የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር እና በአጎራባች በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ምሽግ በማድረግ ጥቃት ለማድረስ በሞከረው ኦነግ ሸኔ ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ የተወሰደውን ርምጃ አስመልክቶ፤ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ሀይልን በመወከል የድሬዳዋ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነር ዓለሙ በመግለጫቸው "ኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን በምዕራብ ሐረርጌ በኩል አቋርጦ በኤረርና ሁርሶ ጀርባ በማድረግ ወደ ድሬዳዋ የገጠር አካባቢዎች ገብቶ ነበር" ብለዋል፡፡

በዚህም ቡድኑ በአስተዳደሩና በአጎራባች ክልሎች በመሠረተ ልማት ብሎም ኢንደስትሪዎች ላይ ጥቃት ማድረስና የብሄር ግጭት ማስነሳት ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑን አመልክተዋል።
ሆኖም ሰባት ንዑሳንን በህብረት ያቀፈው የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ልዩ ግብረ ሀይል ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ በጥንቃቄ ዕቅድ በመንደፍ በልዩ ኦፕሬሽን የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ መቻሉን ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
"ከመስከረም ወር ጀምሮ ጥምር የጸጥታ ግብረ ሀይሉ ባደረገው በዚህ ልዩ ኦፕሬሽን የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድንን በመክበብ ርምጃ ወስዷል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ግብረ ሀይሉ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ በከፈተው ጥቃትም 43 ያህል የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ግብረ ሀይል በወሰደው ስኬታማ ተልዕኮ በምስራቅ ኢትዮጵያ ጥቃት ለማድረስ ሰርጎ የገባውን የቡድኑን ቡድኑ አዛዥ ጃል ሐረርጌ ኢቲመሪ መገደሉንም ኮሚሽነር ዓለሙ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪ የ"ኦነግ ሸኔ" ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሰው የሆኑት ጃል ቦምባስን አቁስሎ፣ እንዲሁም ጃል ራሳን ደግሞ ከነ ሙሉ ትጥቁ መማረካቸውን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የቡድኑ አባላት ከ80 በላይ መሆናቸውን በመግለጫቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ በጥምር የጸጥታ ግብረ ሀይሉ እርምጃ ከተወሰደባቸው 43 ውጪ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት በተቀናጀ መልኩ በተከፈተባቸው ጥቃት ተማርከው እጅ ሰጥተዋል ብለዋል።
ግብረ ሀይሉ የሽብር ቡድኑን ከበባ ውስጥ ከቶ ስኬታማ በሆነ መልኩ በወሰደው የቀጠናውን ሰላም የማረጋገጥ ርምጃ 68 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ 8 ቦንቦች እና ሌሎች መሳሪያዎችን ጨምሮ የወገብ ትጥቆችን መማረክ መቻሉንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

"የኦነግ ሸኔ ቡድን ወደ ምስራቁ ክፍል በድሬዳዋ አስተዳደር ብሎም በሶማሌ ክልል የማህበረሰቡን ሰላም ለማደፍረስ ዕቅድ ነድፎ ለመግባቱ ከበስተጀርባ ድጋፍ ያደረጉ አካላት ነበሩ" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ 34 ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር በማዋል ዘጠኝ መዝገብ መከፈቱንና አራት ያህል መዝገቦችም ለአቃቢ ሕግ መላካቸውን አመልክተዋል።
ኮሚሽነሩ አያይዘውም የኦነግ ሸኔ ቡድን ለቻይና ተቋራጭ የሚሰሩ ሁለት ኢትዮጵያዊያንን በማገት አራት ሚሊየን ብር ተቀብሎ እንደነበርና፤ አካውንቶቹን በማገድ ተባባሪ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አንስተው፤ ጉዳያቸውንም የፌዴራል ፓሊስ ምስራቅ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን እና በድሬዳዋ ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ በጋራ ክትትል እያደረጉበት እንደሚገኝ ነው ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ የተናገሩት።
በአጠቃላይ አሁን ላይ ቀጠናውን ሙሉ ለሙሉ ከኦነግ ሸኔ ቡድን የማጽዳት የጸጥታ ግብረ ሀይሉ ኦፕሬሽን በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ