መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በስፋት እየተተገበረ የሚገኘው የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ባለው የዲጂታል እውቀት ማነስ ምክንያት ሰዎችን ለመጭበርበር እና ያላቸውን ገንዘብ እንዲዘረፋ እያደረገ መሆኑን፤ የምጣኔ ሀብት እና የንግድ ሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
"ገንዘቡን አጭበርብረው ከሰረቁ ግለሰቦች ይልቅ ተጎጂ እየሆኑ እና በስርዓት የሚያስተናግዳቸው አካል እያጡ ያሉት ገንዘባቸው የተዘረፈባቸው ናቸው" የሚሉት የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ከፈለኝ ሀይሉ ናቸው።
"የተዘረፈው ገንዘብ በሕጋዊ ባንኮች እና የክፍያ ዘዴዎች እየተንቀሳቀሰ ነገር ግን ሲያዙ አይታይም" ያሉት አማካሪው፤ ይህ እንዲሆን እያደረገ ያለው ደግሞ ቴክኖሎጂውን አውቆ ከሚጠቀመው በላይ ሌቦች ስለቀደሙ ነው ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት የሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰሩ የመንግሥት ተቋማት ጥብቅ የሆኑ የመረጃ አያያዝ ስርዓቶችን በየጊዜው ማዘመን ይገባቸዋል ሲሉም አክለዋል።
የንግድ ሕግ ባለሙያው አቶ ዳንኤል ፈቃዱ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሮኒክስ ማህተምን እና ጥብቅ የሆነ የመረጃ ደህንነትን ማረጋገጥ ዘርፋ እንዲያድግ ከማስቻሉም ባለፈ፤ ዜጎች እንዲተማመኑበት ያደርጋል ብለዋል፡፡
አክለውም ችግሮች ሲከሰቱ ሕጋዊ ተጠያቂነቶች እንዲመጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
"ማህበረሰቡ የዲጂታል አሰራር ስርዓቱ ላይ እምነት እንዳይኖረው እያደረገው ያለው የአገልግሎት ጥራት ማስነ ነው፤ ይህን ችግር ለመፍታት እና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ተወዳዳሪ እና ጥራት ያለው ገልግሎት ሊያቀርቡ ይገባል" ያሉት ደግሞ በሥራ ክህሎት ሚኒስቴር የገበያ ጥናት እና ትስስር ደስክ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ታደሰ ናቸው።
ከዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚሰሙ የመጭበርበር እና የስርቆት ወንጀሎች ቢኖሩም፤ ዘርፉ ግን አሁን ላይ እያደገ እና ብዙ የአገልግሎት መስኮችም አሰራራቸውን ወደዚሁ ዘርፍ እያስገቡ ናቸው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በዲዲታል የገንዘብ ማጭበርበር ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ከለላ የሚሰጥ መመሪያ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
