መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ የሚገኘው የማሌዢያ ኤምባሲ ከ43 ዓመታት በኋላ ከመስከረም 13 ቀን 2018 ጀምሮ ዳግም ሥራ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የማሌዥያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ኤምባሲው በአዲስ አበባ ዳግም መከፈቱ ማሌዢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጎላ ነው ብሏል።

ኤምባሲው በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ አዳዲስ የትብብር እድሎችን ለመፈተሽ እንደ ማበረታቻ ሆኖ ያገለግላል ሲልም አስታውቋል።

Post image

በዚህም በተለይ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በተጨማሪም ኤምባሲው በአዲስ አበባ ዳግም መከፈቱ ማሌዢያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር እድል እንደሚሰጣት አመላክቷል።

ኤምባሲው በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት ሥራውን እያከናወነ ያለው በሸራተን አዲስ ሆቴል ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።

ማሌዥያ ከአውሮፓውያኑ 1982 ጀምሮ በአዲስ አበባ የነበራትን ኤምባሲ የዘጋች ሲሆን፤ ኤምባሲው በወቅቱ የተዘጋበት ምክንያት በይፋ አልተገለጸም፡፡

ማሌዢያ እ.ኤ.አ. ከ2024 ጀምሮ ወደ 429 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያላት ሲሆን፤ በዓመት 5 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግባለች።

ሀገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2024 አጠቃላይ ወደ ውጭ በላከችው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ በፓልም ዘይት እና ተዛማጅ ምርቶች፣ በፔትሮሊየም፣ በኬሚካሎች እና በማሽነሪዎች የሚመራ 329 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አግኝታለች፡፡ በዚህም ከከፍተኛ የንግድ አጋሮቿ መካከል ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ሆንግ ኮንግ ይገኙበታል።

በተጨማሪም የማሌዢያ እና የኢትዮጵያ የንግድ ልውውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በዚህም እ.ኤ.አ በ2025 ከማሌዢያ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ምርት ወደ 462 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ የተላኩ ምርቶች ደግሞ 273 ሚሊዮን ብር ገደማ ደርሷል፡፡ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚያጠነክር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የማሌዢያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በኢነርጂ እና በማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ