መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ቁማር ቤቶች አድራሻቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

የባለሥልጣሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ በከተማዋ ከ300 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ቁማር ቤቶችን ከፍተው በሚሰሩ በርካታ ሕገ-ወጥ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

ይህም እርምጃ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፤ ሕገ-ወጥ የቁማር አጫዋቾቹ አድራሻቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተግዳሮት እንደሆነበት ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች አካባቢ ፊልም ቤቶች፣ ቁማር ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች ሌሎችም እንደሚከፈቱ አንስተው የክትትል እና የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

‎በየትኛው አካባቢዎች ቁማር ቤት ከፍተው የሚሰሩ ህገ ወጥ ነጋዴዎች እና ግለሰቦችን ህብረተሰቡ ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ