ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 27 ቀን 2017 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላለፉት አምስት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን "የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ" ማሻሻያ ለቋሚ ኮሚቴ መመራቱ የሚታወስ ነው።

ማሻሻያው ያስፈለገው ነጻ፣ ትክክለኛ እና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ እና የሕግ ክፍተትቶችን ለማረም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በ26 አንቀጾች የተደራጀ ነው ተብሏል።

በማሻሻያ ከተካተቱ አንቀጾች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባሎቻቸው 30 በመቶ ገቢ ካልሰበብሰቡ ድጋፍ እንዳይደረግ የሚል ይገኝበታል።

እንዲሁም "በግለሰቦችና በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል 'ስጋት፣ ግጭትን፣ ጥርጣሬን እና አለመተማመንን የሚፈጥር ድርጊት ፈጽሟል' ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምዝገባ እንዲሰርዝ ስልጣን የሚሰጥ አዋጅ መሆኑም ተነግሯል።

አሐዱም ለቋሚ ኮሚቴ የተመራውን የአዋጅ ማሻሻያ በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠይቋል።

የእናት ፓርቲ አባል የሆኑት ጌትነት ወርቁ የተደረገው ረቂቅ የአዋጅ ማሻሻያው ውስጥ የተካተተው 'ፓርቲዎች 30 በመቶ ወጪዎቻቸውን ከአባሎቻቸው ካልሰበሰቡ ድጋፍ አይደረግላቸውም' የሚለው ድንጋጌ ፓርቲዎች ያላቸው አቅም ውስን ቢሆን፤ እራሳቸውን እንዲችሉና እንዲጠንክሩ የሚያደርግ ብሎም ከገዢው መንግሥት ጥገኝነት በጊዜ ሂደት የሚያላቅቅ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል።

"በአንጻሩ ለምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን የማገድ እኛ የመሰርዝ የሚሰጠው ስልጣን ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "በዜጎች መካከል ችግር የሚፈጥሩ ፓርቲዎችን ለማረም በሚጠቅመው ልክ ምንም ያላጠፉ ፓርቲዎችን በመፈረጅ እርምጃ እንዳይወሰድ ያሰጋል" ብለዋል።

የቀደመውን ሃሳብ የሚጋሩት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አመራርና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሙባረክ ረሺድ በበኩላቸው፤ "ቀድሞውንም መንግሥት ለፓርቲዎች ያደርግ የነበረው ድጋፍ ትንሽ ነበር" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ አሁን በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ መቅረቡ ፓርቲዎች ከአባልና ደጋፊዎቻቸው የሚለውን መርህ የሚያጠናክር ተደርጎ መውሰድ እንደሚቻል በማንሳት፤ "በሌላ በኩል ያንን መሰብሰብ ያልቻሉ ፓርቲዎችን ሊያዳክም ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም ፓርቲዎች ግጭት፣ ጥርጣሬና አለመተማመን የሚፈጥሩ ፓርቲዎች መሰረዝ የሚለው ላይ ፓርቲዎች እንዲሻሻል በሚል የሚያወጧቸው መግለጫዎችና የሚያደርጓቸው ንግግሮች በሌላ መንገድ እንዳይተረጎሙ ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በነበረው ስብሰባ ለፓርቲዎች 30 በመቶ ከአባሎቻቸው እንዲሰሰብሱ የሚለው መመሪያ ላይ ድጋፉ ከሚቀር በሰበሰቡት ልክ ድጋፉ ቢደረግላቸው የሚል ሃሳብ ተነስቷል።

እንዲሁም በረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ከዚህ ቀደም ክርክር ሲያስነሳ የነበረው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ለምርጫ በሚወዳደርበት ወቅት ደመወዝ እንዳይከፈለው የሚለውን ድንጋጌ በመቀየር እንዲከፈለው በሚል የተተካ ሲሆን፤ ከምክር ቤት አባላት የግል ድርጅት ሠራተኞችም ላይ ተግባራዊ ቢደረግ የሚል ሃሳብ አንስተዋል።

በተያያዘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከምክር ቤቱ የህግ ክፍል እና ከምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር በዛሬው ዕለት ሐምሌ 02 ቀን 2017 ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደት እራሳቸውን እየቻሉ እንዲሄዱ ለማስቻል ከአባሎቻቸው 30 በመቶ መዋጮ እንዲሰበስቡ የሚያስገድደው ድንጋጌ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴው ከምርጫ ጊዜ ባሻገር ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል።

እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ለሚፈጠሩ ስህተቶች ከማሰረዝ ይልቅ ደረጃ በደረጃ እያረሙና እያስተማሩ መሄድ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደሚያሰፋና የፓርቲዎቹንም በጎ ገጽታ የሚያሳድግ መሆኑ ተገልጿል።

በረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓመታዊ ጉባኤያቸውን ሳያካሂዱ፣ የኦዲት ሪፖርት ሳያደርጉ ሲቀሩና ሌሎች የሥነ-ምግባር ጥሰቶች ሲፈፅሙ ከፓርቲነት እንዲሰረዙ ይደረግ የነበረው ድንጋጌ ተሻሽሎ፤ እንደጥፋታቸው ክብደት መጠን እስከ 5 ዓመት ብቻ እግድ እንዲሆን መደረጉም ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ማሻሻያ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ሴት የግል ተወዳዳሪ 5 ሺሕ አባላት እንዲኖሯት በነባሩ አዋጅ ይደነግግ ነበር በማሻሻያው ወደ 3 ሺሕ ዝቅ መደረጉ ተገልጿል።

ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ ነዋሪነታቸው በሰባት ክልሎች የሆኑ አባላት እንዲኖራቸው የሚለው ሀሳብም ፓርቲዎቹ ሀገራዊ ገጽታ እንዲላበሱ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ለዚህም ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራች አባላት ከሰባት ክልሎች እንዲሆኑ የተደረገበት ምክንያት፣ ቀድሞ የነበረው የአራት ክልሎች ገደብ አሁን ካለው የክልሎች ቁጥር መጨመር ጋር እንዲጣጣም ማድረግን ያለመ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ማሻሻያዎች መካከል፣ አንድ ግለሰብ ለመምረጥና ለመመረጥ የነበረው የ18 እና የ21 ዓመት የዕድሜ ገደብ የምርጫ ምዝገባ ቀንን ሳይሆን የምርጫ ቀንን መሰረት እንዲያደርግ ሆኖ መስተካከሉም ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ