መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸው ቦታዎች ላይ ደመራን መደመር የተከለከለ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።

በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ፖሊስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሁሉም የጸጥታ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዓሉን አስመልክቶ ስልጠና መሰጠቱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለአሐዱ ገልጸዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው በዓል መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ የተለያዩ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ጭምር ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በዚህም መሠረት ለበዓሉ ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን በመግለጽ፤ ከወትሮው በተለየ መልኩ ቴክኖሎጂን ያካተተ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በከተማዋ ያልተሰሩ የኮሪደር ልማቶችን በተመለከተ ደመራ ይደመርባቸው እንደነበረ አንስተው፤ አሁን ላይ ግን የኮሪደር ልማት ከተካሄደባቸው በኋላ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው በመሆኑ እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም ይደመርበት ስለነበረ ብቻ አሁን ላይ ስለማይቻል ሌላ ተለዋጭ ቦታ ላይ በመሄድ ደመራውን መደመር እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ርችት መተኮስ ያጋጥም እንደነበረ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በተከታታይ ዓመታት ግን ለሕብረተሰቡ መረጃ በመስጠት የተቻለ ነገር መምጣቱን አንስተዋል።

በዚህም መሠረት በመስቀል ደመራ በዓል ላይም ርችት መተኮስ ክልክል መሆኑን ተናግረዋል።

Post image

ይህም በመስቀል አደባባይ ብቻ ሳይሆን ደመራዎቹ በሚደመርባቸው አጠቃላይ ቦታዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ በሕገ-መንግሥቱ እውቅና የሌላቸውና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ድርጊቶችን መፈፀም ፍፁም የተከለከለ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የደመራው በዓል በሚከበርበት መስቀል አደባባይ ላይ የፍተሻ ሥራ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ማህበረሰቡ ለዚህ የፍተሻ ሥራ ተባባሪ መሆን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

በተጨማሪም በየአብያተ ቤተክርስቲያናት የሚደረጉ የደመራ ስርዓቶች ሲዘጋጁ በተቻለ አቅም ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ እና የኤሌክትሪክ ፖል ወይም ተቀጣጣይ ነገር በሌለበት ቦታ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎችም የፀጥታ አካላት ሥራ በመከፋፈል በዓሉን ያለፀጥታ ስጋት ለማከናወን ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ የሁሉም በመሆኑ በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ሕብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር ካየ ወዲያውኑ ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ተባባሪ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል።

ከዚህ ሌላ ግን በበዓሉ እለት የትራፊክ መጨናነቅ ያጋጥማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ ፖሊስ የሚዘጉ እና አማራጭ መንገዶችን ይፋ እንደሚያደርግ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ