ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማትና የእንስሳት ተዋጽዖ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገው ዓለም አቀፍ አውደ-ርዕይና ጉባኤ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2018 በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፍቷል።

14ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ (ኢትዮፔክስ)፣ 10ኛው የአፍሪካ እንስሳት ዓውደርዕይና ጉባዔ (አሌክ) እንዲሁም፤ 5ኛው የአፒካልቸር፣ አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርዒት ጥራት ያላቸውን የዘርፉ ዋነኛ አንቀሳቃሾች በማሳተፍ ነው በይፋ የተጀመረው፡፡

Post image

ይህ እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ዐውደ-ርዕይ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ዝቅተኛ የምርት አቅርቦት እና የጥራት ፍላጎት ለመሻገር ያለመ ነው ተብሏል።

በፕራና ኤቨንትስ እና መቀመጫውን ሱዳን ባደረገው አጋሩ ኤክስፖቲም ትብብር የተዘጋጀው ይህ ሁሉን አቀፍ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፤ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ትልቅ መድረክ ነው ስለመሆኑም ተነግሯል።

በዚህ ዐውደ-ርዕይ ላይ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ 100 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች የተገኙ ሲሆን፤ ከ5 ሺሕ በላይ ከኢትዮጵያ፣ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ጎብኚዎችም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Post image

በተጨማሪም በእንስሳት ሀብት እና ጤና ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ውይይቶች ይካሄዳሉ።

በኢትዮጵያ ባህላዊ የዶሮ እርባታ ልምድ በስፋት የሚዘወተር በመሆኑ፤ ዘመናዊ የዶሮ እርባታን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚዘጋጅ ብቸኛው የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኹነት ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ በዘርፉ ያላት ምርታማነትና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከዓለም ዝቅተኛ ነው። ይህ ትርዒት የወተትና የስጋ ዘርፉን በዘመናዊ መልክ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት መድረክ እንደሚሆን ተመላክቷል።

ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ዐውደ-ርዕይና ጉባዔዎች ለዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተትና ሥጋ ንዑስ ዘርፎች ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው ተገልጿል።

የፕራና ኢቨንትስ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሜሮን ሰሎሞን እንደተናገሩት፤ እነዚህ ኹነቶች ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለንግዱ ማኅበረሰብ ትልቁ መሰባሰቢያ በመሆናቸው፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና የእውቀት ሽግግር በማምጣት ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

Post image

በሌላ በኩል፣ የዓለም ምግብ ድርጅት ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የእንስሳት ሀብት ባደጉት ሀገራት 40 በመቶ ገደማውን፣ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ደግሞ 20 በመቶውን የግብርና ምርት ይሸፍናል። እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝቦችን ኑሮ እንደሚደገፍ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት የእንስሳት ተዋጽዖ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት በሚፈለገው መጠንና ጥራት የፍላጎቱን ያህል ማድረስ አለመቻሉን ተከትሎ፤ ይህ ዐውደ-ርዕይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የንግድ ትርዒቱ የግብርና ሚንስትር አማካሪ አለማየው መኮንን (ዶ/ር)ን ጨምሮ፤ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የንግድ ጎብኚዎች ተገኝተዋል።

Post image

የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ዓውደርዕይና ጉባዔ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ባለቤት መሆኗ ባያጠራጥርም በዘርፉ ያላት ምርታማነት እና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከዓለም ዝቅተኛ ነውም ተብሏል፡፡

ይህ የንግድ ትርዒትም የወተት እና የስጋ ዘርፉን በዘመናዊ መልክ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት መድረክ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ