ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋናውን የባቡር ትራንስፖርት መሠረት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማዳረስ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

ከእነዚህም መካከል በቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ለሶፍ ዑመር ዋሻ መሆኑ ተገልጿል።

Post image

ኮርፖሬሽኑ ይህን ሥራ የጀመረው ሀገር ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።

የባቡር ትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ስለሺ ካሣ (ኢ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ሶፍ ዑመር ዋሻ ከሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ቅድሚያ የተሰጠው በዋሻው ግዝፈት እና በዋሻው ዙሪያ እየተካሄዱ ባሉ ጥናቶች ምክንያት ነው።

ኢንጂነር ስለሺ አክለውም፤ በአካባቢው ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች በመንግሥት ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የቱሪስት እንቅስቃሴ እንደሚኖር ይጠበቃል ብለዋል።

Post image

የባቡር ትራንስፖርቱ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በተጨማሪ፤ ሌሎች አማራጭ ትራንስፖርቶች ዋሻውን እንዳይጎዱ ለመከላከልም ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ የትኛው የቱሪስት መስህብ የባቡር ትራንስፖርት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል ጥናት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው፤ "ለማንኛውም የቱሪዝም እንቅስቃሴ የትራንስፖርት ዘርፉ አመቺ መሆን የተሻለ የቱሪስት እንቅስቃሴ ይፈጥራል" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ