መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ከቬንዙዌላ ከባህር ዳርቻዎች 75 ኪሜ ርቀት ላይ መስፈራቸውን ተቀባይነት የለውም ሲል በኢትዮጵያ የቬንዙዌላ ኤምባሲ ድርጊቱን አውግዟል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአሜሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ቬንዙዌላ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየሻከረና የአሜሪካም በሀገሪቷ አቅራቢያ ጦር ማስፈር መጀመሯ እየተገለጸ ይገኛል።

በዚህም ከትናንት መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አሜሪካ የጦር አውሮፕላኖቿን በባህር ዳርቻዎች አቅራቢያ በሚገኘው የአየር ክልል በ75 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ማስፈሯን ቬንዙዌላ የማትቀበለው መሆኑን በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ይህ ድርጊት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና የቺካጎ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ስምምነትን የጣሰና የሀገር ሉዓላዊነትንም አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል ኤምባሲው ገልጿል።
እንዲሁም የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በአቅራቢያው መስፈራቸው በካሪቢያን ባህር ላይ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ፣ የሲቪል እና የሥራ ደህንነትን በእጅጉ አደጋ ላይ ጥሏል ብሏል።
"ይህን መሰል ትንኮሳ የቬንዙዌላ መንግሥት አይታገስም" ያለው መግለጫው፤ የአሜሪካ መንግሥት የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ቀጠናን ለማፍረስና አለመረጋጋት ውስጥ ለመክተት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሊያቆም ይገባል ሲል አሳስቧል።

የቦሊቫሪያ መንግሥት ቅሬታውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ለዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) እና ለላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ግዛቶች (CELAC) ማህበረሰብ ያቀረበ ሲሆን፤ ይህንን ህገወጥ ድርጊት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃዎች የሚወሰዱ መሆኑን ኤምባሲው ጠቁሟል።
ስለሆነም የቦሊቫሪያ ብሔራዊ ጦር ሃይል በዘላቂነት ንቁ ሆኖ ለመቆየት ከኤሮስፔስ መከላከያ ሲስተም ጋር በጋራ ይሰራል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
አሜሪካን ከቬንዙዌላ ዕፅ ዝውውር ስጋት ነፃ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖችን በመደገፍ አሜሪካን የኮኬይን መናኸሪያ ለማድረግ እየሰሩ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።

በዚህም ምክንያት አሜሪካ "ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚረዳ መረጃ ለሚያቀርብልኝ የ50 ሚሊየን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ" ማለቷ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የአሜሪካን F-35 ተዋጊ ጀቶች በቬንዙዌላ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ መታየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ድርጊቱ የአሜሪካ ወታደራዊ ትንኮሳ እና የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው ሲል የሀገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ