መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎መደበኛ ባልሆነ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በማያውቁት ሀገር ለውትድርና እየተመለመሉ ነው ሲሉ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሕገ-ወጥ ፍልሰተኞቹ ከሚያጋጥሟቸው የከፉ ችግሮች መካከል፤ እሥር፣ የወሲብ ባርነት፣ መደፈር፣ ከባድ አካላዊ ቅጣት፣ አካል ጉዳተኝነት፣ እንደ ኩላሊት ያሉ የውስጥ አካልን በግዳጅ መዘረፍ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ከሀገር የሚወጡት ዜጎች ከአካል ጉዳት እና የግዳጅ ውትድርና በተጨማሪ፤ ለአዕምሮ ጤና እክል እና ለሥነ-ልቦና ቀውስ ተጋላጭ እንደሚሆኑም ተነስቷል።

ሚኒስትር ደኤታዋ አያይዘውም፤ የሰው ልጅ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ፍላጎቶችን ለማጣጣም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሱ ግድ ቢሆንም፤ እንቅስቃሴው ሕጋዊ መስመርን ካልተከተለ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አብራርተዋል።

መንግሥት መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር በተቀናጀ መልኩ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፤ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች ከተደራጁ ሕገ-ወጦች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ሕገ-ወጥ ደላሎች ከሕብረተሰቡ የተሸሸጉ እንዳልሆኑ ጠቁመው፣ ዜጎች ሕገ-ወጦችን በማጋለጥ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም፤ መንግሥት ለችግር ተጋላጮች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ከስደት ተመላሾችንም መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ከአውሮፓ ሕብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከጤና ሚኒስቴር እና ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር ይፋ ባደረገው መመሪያ መሠረት በተለይም የአዕምሮ ጤና እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከስደት ተመላሾች እርዳታ እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

መመሪያው ለተጎጂዎች እና ተጋላጭ ፍልሰተኞች የሚሰጡ የአዕምሮ ጤና፣ የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎቶች እንዲሁም፤ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስቴር ደኤታዋ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ