ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በድሮው ሆለታ ገነት በአሁኑ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ቅጥር-ግቢ ውስጥ የሚገኘውን የቤተ-መንግሥት ሕንጻ ለመጠገን እና ለማደስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተድርጓል፡፡
የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ዓርበኞች ማህበር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው እድሳቱን ለማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያዩት።

የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስ እና ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ፤ ይህንን ታላቅ ቤተ-መንግሥት ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከር አሥፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅርሱ ሙሉ ለሙሉ ከመታደሱ በፊት አሁን ያለውን ሕንጻ መታደግ ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ዓርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይህንን ጥንታዊ እና ታሪካዊ የቤተ-መንግሥት ሕንጻ ተንከባክቦ ለትውልድ ማስተላለፍ ታላቅ ሀገራዊ ሃላፊነት በመሆኑ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንጻ እና የስነ- ቁፋሮ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታደሰ ግርማ፤ ከጃፓኑ ሽባውራ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጠቀም በጋራ ለመስራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱም ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ጃፓን እና ከጃፓን ወደ አዲስ አበባ የመስክ ጉብኝት እንዳደረጉም አስታውሰዋል
ይህንን የቅርስ ጥናት፣ ጥገና እና እደሳ ለማከናወን ከጃፓን ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ ለመጠቀም መስማማታቸውንም ባሙያው ገልጸዋል፡፡
የኪነ-ሕንጻ ባለሙያው አቶ ታደሰ የግል ሕይወታቸውን ወደ ኋላ በማለት ሌሎች በሕይወት መኖር እንዲችሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ ከሚያቆሙ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ መስራት ታልቅ ኩራት ነውና ከመከላከያ ጋር በመስራታችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በቅርሱ ዙሪያ መረጃ ለመሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን መረጃ ዶክመንት ለማድረግ፣ ቅርሱ የደረሰበትን ጉዳት ለማጥናት፣ ጥገናውን ለማከናወን እንዲሁም ሙሉ ህንፃውን ለማደስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 