ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለመዝናኛ ስፍራ ግንባታ የተለዩ ቦታዎች የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ከመድፈን ይልቅ ባሉበት ሁኔታ ለቀጣይ ልማት እንዲዘጋጁ መወደኑ ተገልጿል።
አስተዳድሩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ጉድጓዶቹን ለመድፈን የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እና መልሰው የሚቆፈሩ ከሆነ የሚኖረውን ብክነት ለመከላከል ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የስርዓተ-ምህዳርና ብዝኃ-ሕይወት አያያዝ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ይታገሱ እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ የማዕድን ማውጣት ፈቃድ አልሚዎች ሥራቸውን ሲጨርሱ ቦታውን መልሰው እንዲደፍኑ የሚያስገድድ ቢሆንም፤ ቦታዎቹ በከተማዋ ማስተር ፕላን ውስጥ ለሕዝብ መዝናኛ እንዲሆኑ ከተለዩ፣ የመድፈኑ ሥራ ተትቶ ለቀጣይ ልማት እንዲዘጋጁ ይደረጋል።
ዳይሬክተሩ ይህ ውሳኔ ጉድጓዶቹ በማዕድን አልሚዎች ቢደፈኑም ተመልሰው ሊቆፈሩ ስለሚችሉ፣ ለማስተካከል የሚወጣውን በጀት ለመቀነስ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የማዕድን ማውጣት ፈቃዱ ቦሌና ለሚ ኩራን ጨምሮ በ5 ክፍለ ከተሞች እንደሚተገበር አንስተዋል።

ቦታዎቹ ሳይደፈኑ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመለጠፍና ማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለመስጠት ተደጋጋሚ ሥራዎች እንደሚሠሩ አቶ ቴዎድሮስ አብራርተዋል።
ከዚህ በፊት ተቆፍረው ጥበቃ እየተደረገላቸው ያሉ ቦታዎች እንዳሉ አስታውቀዋል።
የማልማቱ ሥራ እንዳለ ሆኖ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የማይወጡና ግዴታቸውን የማይፈጽሙ አልሚዎች ላይ ግን ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 