ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ኬፕታውን ከተማ የሚገኘው የፋይናንስ ቁጥጥር እና ማካተት ማዕከል (ሴንፍሪ) ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ ከ107 ሚሊዮን በላይ "የሞባይል ገንዘብ" አካውንቶች መመዝገባቸውን ገልጿል።

የባንክ ደብተር ሳይኖር በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ገንዘብ መላክ፣ መቀበል እና ማስቀመጥ የሚያስችለው "የሞባይል ገንዘብ” አገልግሎት በኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት ዕያሳየ እንደሆነ ያመላከተው ይህ ጥናት፤ "ሀገሪቱ ወደ ዲጂታል ክፍያና ኢንሹራንስ አገልግሎቶች ለመሸጋገር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለች ነው" ብሏል።

ሴንፍሪ በ2024-2025 ባካሄደው ጥናት 9 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አዋቂዎች የባንክ አካውንት ሳይኖራቸው በሞባይል ገንዘብ አገልግሎቶችን እየተገለገሉ እንደሆነም ገልጿል።

የተቋሙ ቴክኒካል ዳይሬክተር ክሪስቲን ሁጋርድ በኢትዮጵያ የተመዘገበውን የሞባይል ገንዘብ እድገት አስመልክተው ለአሐዱ ሬዲዮ ሲናገሩ፤ "ይህ እድገት ለዲጂታል ክፍያ አሰባሰብ እና ለመድኅን አገልግሎት ጠንካራ መሠረት ይፈጥራል። እስከ 58 ሚሊዮን የሚደርሱ ዋስትና የሌላቸው አዋቂዎች በዲጂታል ወይም በተደራጁ አውታረ መረቦች መድረስ ያስችላል" ብለዋል።

Post image

ይህ የሞባይል ገንዘብ ስርጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የባንክ አገልግሎት ያልደረሳቸውን ዜጎች በቀላሉ ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ ለማካተት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ሆኖም ጥናቱ፤ ኢንዱስትሪው አሁንም በግሉ ዘርፍ እና በዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች መካከል ጠንካራ አጋርነት አመላክቷል። ይህ መሆኑ የእድገቱን ፍጥነት ሊገታው የሚችል ክፍተት በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ምክረ-ሐሳብ ተሰጥቷል።

የሞባይል ገንዘብ ማለት የባንክ ሂሳብ ደብተር ሳይኖር፣ በሞባይል ስልክ አማካኝነት ገንዘብ መላክ፣ መቀበል እና ማስቀመጥ የሚቻልበት መንገድ ሲሆን፤ በአፍሪካ፣ በእስያ እና በሌሎች አካባቢዎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ