መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማቱ ላይ የተሰራ የትራፊክ ምልክት ነቅለው የወሰዱ ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር ውለው በ6 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ በኮሪደር ልማቱ ላይ ከተተከለው የትራፊክ ምልክ በተጨማሪ 6 የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን (Dust bins) መስረቃቸውንም በምሪት ማሳየታቸውንም ፖሊስ ገልጿል፡፡

Post image

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡00 ሠዓት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ካምብሪጅ ትምህርት ቤት አካባቢ ነው፡፡

ተከሳሾች ታረቀኝ ታፈሰ እና አፈወርቅ ዮናስ በኮሪደር በለማ መንገድ ላይ ተተክሎ የነበረ የመንገድ ዳር የትራፊክ ምልክት ነቅለው ይዘው ሲሄዱ፤ በወቅቱ በወንጀል መከላከል ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ፖሊስም ተከሳሾችን ይዞ ባደረገው ምርመራን የማስፋት ተግባር በኮሪደር በለማ መንገድ ላይ ዳር ተቀምጦ የነበረ የዋጋ ግምታቸው 200 ሺሕ ብር የሚያወጣ 6 የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን (Dust bins) በመስረቅ በአካባቢው ለሚገኙ 3 ተቀባዮች በ8 ሺሕ ብር የሸጡ መሆኑን አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን ገልጿል፡፡

Post image

ይህንንም የተከሳሾች ቃል በመያዝ ተቀባዮችን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ኤግዚቢቶቹን ማስመለስ መቻሉን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾች ታረቀኝ ታፈሰ እና አፈወርቅ ዮናስ በፈፀሙት የትራፊክ ምልክት የስርቆት ወንጀል፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

በቀጣይም በፈፀሙት የመንገድ ዳር የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን (Dust bins) ስርቆት ወንጀል ለውሳኔ ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ/ም እንዲቀርቡ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሕዝብ ሀብት ላይ የሚፈፀሙ በመሆናቸው፤ ሕብረተሰቡ መሠል የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት ለአቅራቢያው የፀጥታ አካል መረጃ ሊሰጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።

አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ