ሰኔ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ስኬት ላይ የሚያጠነጥነው "የኃይሌ ኃይሎች (DiSSECTING HAILE) የተሰኘው መፅሃፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡

በባለታሪኩ ልጅ ሜላት ኃይሌ የተደረሰውን አዲሱን መጽሐፍ አስመልክቶ በዛሬው እለት በኃይሌ ግራንድ መግለጫ ተሰጥቷል።

የጀግናው አትሌት ሺ አለቃ ኃይሌ ገብረ-ስላሴን ሕይወት የሚያስቃኘው ይህ መጽሐፍ በውስጡ ከኃይሌ ስኬቶች ጀርባ ያሉ በርካታ ምስጢሮችን ይዟል ተብሏል።

Post image

መጽሐፉ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከእረኝነት ዘመኑ አንስቶ ያለውን ሕይወት፣ መርሆች እና የስኬት ጉዞን የሚዳስስ ሲሆን፤ ይበልጥ ትኩረሩን በአትሌቱ የሕይወትና የሥራ ፍልስፍና ላይ እንዳደረገም ተነግሯል።

የመጽሐፉ ደራሲ ሜላት ኃይሌ "መጽሐፉን ለመጻፍ ከአንድ ዓመት በላይ ወስዶብኛል" ያለች ሲሆን፤ በውስጡ የተባሉት ነገሮችን በሙሉ ባለታሪኩን አባቷንና እናቷንም ጭምር በመጠየቅ ያለአድሎ መጻፏን ተናግራለች።

"እኔ የተግባር እንጂ የወሬ ሰው አይደለሁም" ያለው ሻለቃ ኃይሌ በበኩሉ፤ ልጁ መጽሐፉን ስትፅፍ ለምትጠይቀው ጥያቄ ተገቢውን መልስ እና ማብራሪያ መስጠቱን ገልጿል።

መጽሐፉ በ12 ምዕራፎች የተቀነበ ሲሆን፤ በውስጡም 12 የኃይሌን ፍልስፍናዎች ይዟል ተብሏል።

Post image

በልጁ ሜላት ኃይሌ የተደረሰው ይህ አዲስ መጽሐፍ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንዲሁም በብሬል መዘጋጀም የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይ ነሐሴ ወር ላይ ተመርቆ ለንባብ ይበቃል ተብሏል።

መጽሐፉ ሲመረቅ በአማዞን፣ በቴሌብር፣ በተለያዩ የኦንላይን አማራጮችና እንዲሁም መጽሐፍት መሸጫ መደብሮች ላይ እንደሚቀርብም ተመላክቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ