ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሁንም በቂ ትኩረት ባለማግኘታቸው ምክንያት ሴቶችና ሕፃናት ከፍተኛ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን አሳሰበ።

ማኅበሩ ይህን የገለጸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ባዘጋጀው፤ የ16 ቀን የፀረ-ጾታ ጥቃት ዘመቻ መጀመርን አስመልክቶ በተካሔደ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

Post image

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ተወካይ ሰላማዊት ካሳዬ፤ ማኅበሩ በወንጀል እና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ዙሪያ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። "በቤት ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት (Domestic Violence) አሁንም ትኩረት እየተሰጠው አይደለም" ብለዋል፡፡

የማኅበሩን ድጋፍ የሚጠይቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በብዛት ከሚመጡ ጉዳዮች መካከል ሴቶች በእምነት ውክልና በመስጠት ያላቸው ንብረት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህ መሰል ጉዳዮች የሚመጡት ንብረት በሌላ ሰው ሥም ከሆነና ጊዜው ከረፈደ በኋላ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በቤተሰብ መካከል "ቀለብ ይወሰንልኝ" ጥያቄ ይዘው የሚመጡ ሴቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። ይሁንና ማኅበሩ ያለው አቅም በቀን 30 ሴቶችን ብቻ ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ ሀሳብ የሰጡት ከሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር ከፍተኛ የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ሌንሳ ካሳሁን በበኩላቸው፤ "የተማረችም ሆነች ያልተማረች ሴት ለጥቃት ተጋላጭ ናት" ብለዋል።

ከ2 ዓመት ሕጻናት ጀምሮ እስከ 70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አረጋውያን ድረስ ጥቃት ደርሶባቸው ለድጋፍ ወደ ማኅበሩ እንደሚመጡ አስረድተዋል።

ከ13 እስከ 18 ዓመት ያሉ ታዳጊ ወጣቶች በስፋት ከሚመጡት መካከል እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ጦርነት በነበረባቸው እና አሁንም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ባህሪው የተለየና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን አንስተዋል። ማኅበሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሴቶች መጠለያ፣ የማማከር አገልግሎት እና ትምህርት በመስጠት ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው፤ መገናኛ ብዙኃን ችግሩን ከማሳየት ባሻገር መፍትሔውን ማመላከትና መከታተል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የፓናል ውይይቱ የተካሔደው ትናነት ሕዳር 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል፣ ፖሊስ፣ የሕግ አካላት እና በሥርዓተ ጾታ ዘርፍ ላይ አተኩረው የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል። የፀረ-ጾታዊ ጥቃት መከላከል የንቅናቄ ቀናት ከኅዳር 16 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ይከበራሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ