መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)በአፍሪካ አህጉር የሚደረገው የእርስ በርስ የንግድ ለውውጥ ገና ያልተሰራበትና ከ17 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል።

በነገው ዕለት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን በይፋ የምትጀምር መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ አሁን የተደረሰው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በሀገራቱ መካከል የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

ሌላው የአህጉሩ ሀገራት ከሌሎች ጋር የሚደርጓቸው የንግድ እንቅስቀሴዎች 67 በመቶ ሲደርስ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የእርስ በርስ ንግድ ግን ከ17 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የምታደርገው ንግድ ዝቅተኛ ሆኖ በአንፃሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ልውውጥ የተሻለ የሚባል መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ስምምነት የሀገራቱን የንግድ እንቅስቃሴ የሚጨምር መሆኑን ጠቁመዋል።

በስምምነቱ ውስጥ ከ55 በላይ ሀገራት መኖራቸውን ገልጸው፤ ከ1 ነጥብ 4 ቢልየን በላይ ሕዝብ ያቀፉ፤ ከ3 ነጥብ 4 ትሪልየን ዶላር ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት የሚበልጥ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የዚህ ከባቢያዊ ውህደት መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ጠቀሜታም በሀገር ውስጥ ላሉ ላኪዎች፣ አምራቶች፣ ሴቶችና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ምርቶች ከፍተኛ የሆነ ወጪን መቀነስ፣ ታሪፍ ነክ ያልሆኑ ችግሮች ለመቀነስና የንግድ ወጪን ለመቀነስ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ስምምነት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

Post image

ይህ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለሸማቾች ሰፊ አማራጮችን መፍጠር፣ የዜጎች የገቢ መጨመርም የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለኢንቨስተሮች በሚፈጠረው ዕድል የሀገራትን ሳይሆን በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሸማች ቁጥር እና መዳረሻ የሚያሰፋ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ይህ ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈረመው በሩዋንዳ ኪጋሊ በአውሮፓውያኑ 2018 መሆኑና ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ፈራሚ መሆኗን ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስሚን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ