ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰመራ ሎጊያ ከተማ ከሕዳር 6 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 10ኛው የከተሞች ፎረም ተከትሎ፤ ከሰሞኑ በአፋር ክልል በዞን ሁለት መጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ዋራዓ እና ሚልኪ በሚባሉ አካባቢዎች የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለፎረሙ መካሄድ ምንም አይነት ስጋት እንዳልሆነ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

"በክልሉ አንድ ቦታ ላይ ችግር ሲፈጠር ሙሉ አፋር ላይ እንደተከሰተ ወይም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የሚያዳረስ አድርጎ ማሰብ አለ" የሚሉት የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሀመድ ያዮ ናቸው።

ነገር ግን ከሰሞኑ የፀጥታ ችግር የተፈጠረበት ቦታ እና ፎረሙ ከሚካሄድበት ሎጊያ ከተማ እስከ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት መኖሩን በማንሳት፤ ከዛ በተረፈ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዳለ ገልጸዋል።

Post image

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ችግሩ የተከሰተበት ቦታ የወረዳው ማዕከል እንኳ ሰላም ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም ፎረሙን ለማዘጋጀት ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ በመግለጽ፤ ፎረሙን ለማካሄድ የሚያስችል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ለእንግዶች የሚመጥን ቦታን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ በከተማዋ የሚጎበኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማስጎብኘትና ለማስተዋወቅ እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሆቴሎች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማፅዳት መልካም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተመቻቸ እንደሆነ አክለዋል።

Post image

150 የሚሆኑ ከተሞች የሚሳተፉበት ፎረም መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን ዕድል በመጠቀምም ከሎጊያ ከተማ ባሻገር አጠቃላይ የአፋርን ባህልና ቱሪዝም በተለያየ ሁኔታ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በገቢ ደረጃ 'ይሄን ያክል' ተብሎ በግልፅ የተቀመጠ ቁጥር አለመኖሩን በማንሳት፤ ነገርግን የሚመጡ እንግዶች እስከ 5 እና 6 ቀን ሊቆዩ ስለሚችሉ የተሻለ ገቢን ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ