ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ወረዳዎች ለሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ካቋረጡ አራት ዓመት እንደሞላቸው የዞኑ መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

መምሪያው አሁንም በክልሉ በቀጠለው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው በዞኑ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የአስፋልት መንገዶች ለሕዝብ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ መንገዶቹም ከጃናሞራ ወደ ደባርቅ፣ ከበይዳ ወደ ደባርቅና ከጠለምት ወደ ደባርቅ ያሉት የአስፋልት መንገዶች መሆናቸውን ጠቁሟል።

በዚህ ምክንያት፤ ምንም አይነት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኗል፣ ነፍሰጡር እናቶች ድንገተኛ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዳይጠቀሙ ዳርጓል እንዲሁም መድኃኒት፣ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን ወደ ወረዳዎቹ ማስገባት አልተቻለም ብሏል።

ቢሮው መንገዱ እንዲስተካከል ለክልሉ የመንገዶች ባለስልጣን በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረብን ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠን አልቻለም ሲልም ነው ለአሐዱ የገለጸው።

አሐዱ የዞኑን ቅሬታ በመያዝ ለክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ቢያደርግም፤ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ከባለስልጣኑ ምላሽ ባገኘ ሰዓት በዘገባ ሽፏን የምንመለስ ይሆናል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ