ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በተለምዶ "ሿሿ” የተባለውን ወንጀል በመፈፀም ሞባይል ስልክ ሰርቀው ለማምለጥ ሲሞከሩ በተያዙ 7 ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ሤራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ናትናኤል አለሙ፣ አቤል ኮርሳ፣ ዕድላዊት መላከ፣ መቅደስ አቡሽ፣ ኢዛና ባህሩ፣ ፀጋ ታደሰ እና መቅደስ አምዴሳ የተባሉ ሲሆኑ፤ ሽፈራው ገበየሁ በተባለ ግለሰብ ላይ ወንጀሉን የፈፀሙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ኮዬ ቂሊንጦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ተጠርጣሪዎቹ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 89261 ኦ.ሮ በሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው የግል ተበዳይን ጭነው እየተጓዙ ሞባይል ስልኩን ከኪሱ ከሰረቁ በኋላ፤ "ትራፊክ ይቀጣናል ጋቢና ግባ ብለው" እንዳስወረዱት እና ከወረደ በኋላ ጥለውት እንዳመለጡ ተገልጿል፡፡
በግል ተበዳይ ላይ ወንጀል እንደተፈፀመ የተመለከቱ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ክትትል ወንጀሉን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 5 ሴቶች እና 2 ወንዶች ሳሪስ አቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ ከተሽከርካሪው ወርደው ሊሰወሩ ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ነው ፓሊስ የገለጸው፡፡

በወቅቱ በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻ ከተለያዩ ግለሰቦች ላይ በተመሳሳይ መልኩ የተሰረቁ ዘጠኝ ሞባይል ስልኮች መያዛቸውም ተነግሯል
በዚህም መሠረት የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጀመረውን የምርመራ ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በተጠቀሰው ተሽከርካሪ እና በተያዙት ተጠርጣሪዎች 'ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞብኛል' የሚል ግለሰብ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመቅረብ ከተያዙት ስልኮች መካከል የእሱ ንብረት ስለመኖሩ በማረጋገጥ እንዲወስድ እና ለፖሊስ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ