ጥቅምት 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ስለ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ መኖሩን ቢገልፁም፤ የሕግ ባለሙያዎች ግን የፍትሕ ተቋማቱ ገለልተኝነት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን በመጥቀስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራበት አሳስበዋል፡፡

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በሕገ መንግሥቱ "ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ናቸው" የሚል አንቀጽ ቢቀመጥም፣ በተግባር ግን በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ ስለዚህም መንግሥት የፍትሕ ተቋማትን ገለልተኝነት ባከበረ መልኩ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ለዚህም በመንግሥት በኩል፤ "የተቋማቱን ገለልተኝነት በጠበቀ መልኩ የአቅም ግንባታ መስራት፣ በቂ በጀት መመደብ እና ምቹ የሥራ ከባቢን መፍጠር አስፈላጊ ነው" ያሉ ሲሆን፤ የፍትሕ አካላትም ኃላፊነታቸውን በትክክል መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ፍርድ ቤት ዜጎች እምነት የሚጥሉበት ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ በተሰጣቸው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሰረት ፍትሐዊ ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበባው አበበ የአቶ ጥጋቡን ሐሳብ በመጋራት፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥትና ከፍትሕ አካላት የሚጠበቅ ዋና ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።

ኃላፊነት ያለባቸው የፍትሕ ተቋማት አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ካልቻሉ፤ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ በሕጉ መቀመጡን ገልጸዋል።

አቶ አበባው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ያስቀመጣቸው መመሪያዎች በትክክለኛው መንገድ ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፤ ስለሆነም ዜጎች ሕጉ የሰጣቸው መብት እንዲተገበር፣ ክፍተቱ ያለው የቱ ጋር እንደሆነ በግልጽ ሊለይ ይገባል ብለዋል።

በሕጉ በግልጽ ከተቀመጠና የአፈጻጸም ክፍተት ካለ፤ በምን መልኩ መፍታት ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ መስራት ይገባል ይሉም ሲሆን፤ መንግሥትና ሕግ አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሊያደርጉበት እንደሚገባ አንስተዋል።

የዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት (World Justice Project) ጥናት ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ገልጿል።

ጥናቱ እንዳመለከተው፣ በ2025 የዓለም ፍትሕ ፕሮጀክት የሕግ የበላይነት መለኪያ (Rule of Law Index) ከ143 ሀገራት ኢትዮጵያን 132ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

የሀገሪቱ ነጥብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ2 ነጠብ 4 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ ሪፖርቱ ይህ መዳከም ባለፉት 5 ዓመታት የተቋማት መዳከም እና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በስፋት መኖሩን ያሳያል ሲል ገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ