ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ ትራንፖርት ቢሮ በአየር ማረፊያ አካባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች፤ በቋንቋ እና በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
ቢሮው የትራንስፖርት አገልግሎቱ ለዜጎች ተደራሽ እና ዘመናዊ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጸው፡፡
በትራንስፖርት ቢሮው የሕዝብ ትራንስፖት ስምሪት አደረጃጃት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ስዩም፤ አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት እና ብዛት ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ከተማዋ የሚስተናገዱባት በመሆኗ፤ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማዘመን እንደሚገባ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ገለጸው፤ አገልግሎቱ ታሪፍን መሠረት ያላደረገ እና በአሽከርካሪ እና በደንበኛው አማካኝነት በድርድር የሚናወን የትራንስፖርት ክፍያ ሲፈጸም እንደሚስተዋልም አንስተዋል፡፡
ቋንቋን፣ አለባበስን፣ ሥነ-ምግባርን እና የተሸከርካሪ ደረጃን መሠረት ያደረገ መመሪያ ከዚህ ቀደም ስለመኖሩ የገለጹም ሲሆን፤ ቢሮው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ በአየር መንገድ አካባቢ የሚሰጠውን የትራንስፖርት አገልግሎት ማዘመን እና ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የክፍያ ዋጋን ጨምሮ የሚሰጠው አገልግሎት በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሕዝብ ትራንስፖት ስምሪት አደረጃጃት ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በ2009 ዓ.ም. በወጣው መመሪያ መሠረት አቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂ.ፒ.ኤስ)ን ጨምሮ ሌሎችንም በመመሪያው የተዘረዘሩ ግዴታዎች ባልተገበሩ የሜትር የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የእግድ ደብዳቤ መጻፉን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በመመሪያው የተዘረዘሩት ግዴታዎች መካከል፤ ለተሸከርካሪ፣ ለአሽርካሪ እና ለተሳፋሪ ኢንሹራንስ መግባት፣ ተሽከርካሪው የመጀመሪያ ዕርዳታ ከጥሪ ማዕከል ጋር የተገናኘ እንዲሆን፣ የተሸከርካሪው ቀለም ግልጽ እንዲሆን፣ የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒኤስ) በተሸከርካሪው ላይ እንዲገጠም እንዲሁም፤ በኪሎ ሜትር የተመሠረተው የክፍያ ተመን በዲጂታል የክፍያ ስርዓት ሊዘረጋለት ይገባል የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በዚህም መሠረት በሜትር ታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙና መመሪያው የሚያዘውን ቅድመ ሁኔታ ያላሟሉ አሽከርካሪዎች፤ የሥራ ፈቃዳቸው እንደማይታደስ ዳይሬክተሩ ከአሐዱ ራድዮ ሁሉ ደህና ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
የወጣውን መመሪያ ማስከበር የተቋሙ ኃላፊነት እንደሆነ እና መመሪያውን ለማስተግበር ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተናገሩም ሲሆን፤ "ለአብነትም ያህል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ተጠቃሽ ነው" ብለዋል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ያቆብ ማሞ በበኩላቸው፤ የታክሲ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ ሀገራት ተሞክሮ እና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መመልክት ተገቢ እንደሆነ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በአንድ ተቋም ሥር በመሆን እና ታክሲው ሊያሟላቸው የሚችሉ የደረጃ መስፈርቶች ተዘጋጅተው እንደሚገኙ የገለጹት ባለሙያው፤ የዓለም አቀፉን ተሞክሮ ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የተቋም ፈቃድ ሳይኖራቸው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፉን ማስተካካል ተገቢ በመሆኑ፤ ደንብ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
"ይህም ደንብ በስታንዳርድ ላይ ያለውን ክፍተት የሚፈታ እንዲሁም በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙና የሜትር ታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተሸከርካሪዎች በሕግ ማዕቀፉ ውስጥ እንዲገቡ ያስችላል" ብለዋል፡፡
የደንበኛን እንዲሁም የአሽከርካሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የተገለጸም ሲሆን፤ ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲካተቱ አስቻይ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአየር ማረፊያ አከባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች በቋንቋ እና በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ
የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂ.ፒ.ኤስ)ን ጨምሮ መመሪያውን በጣሱ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የእግድ ደብዳቤ መጻፉ ተነግሯል
