ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በተለያዩ የደረጃ ምዘና ችግሮች ምክንያቶች አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸው የተዘጉ ትምህርት ተቋማት፤ ለቀጣይ ዓመት በአዲስ ፍቃድ መመዝገብ እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
ባለስልጣኑ 'ትምህርት አሰጣጣቸው ከተቀመጠው ደረጃ በታች ነው' ባላቸው 28 የትምህርት ተቋማት ላይ በወደሰው አስተዳደራዊ እርምጃ ፈቃዳቸው መሰረዙ ይታወሳል።

የትምህር ተቋማቱ በ2016 ዓ.ም ማጠቃለያ ላይ በተደረገው የእድሳት ፍቃድ ምዘና ለ2017 የትምህርት ዘመን ካሳዩት ዝቅተኛ ውጤት መሻሻል እንዲያሳዩና በማስጠንቀቂያ እንዲያስተምሩ ጊዜ ቢሰጣቸውም፤ በታኅሣስ 2017 ዓ.ም በተደረገ የእድሳት ፍቃድ ምዘና ውጤታቸው መሻሻል ባለማሳየቱ እንዲሁም ዝቅተኛና ከደረጃ በታች በመሆኑ በ2018 የትምህርት ዘመን ማስተማር የማይችሉና እውቅናቸው የተሰረዘ መሆኑ መገለጹም አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም በተገኘባቸው ጉድለት ምክንያት ፈቃዳቸው የተሰረዘው ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ደረጃ ሟሟላት ከቻሉ፤ ለ2018 የትምህርት ዘመን በአዲስ ዕውቅና እና ፈቃድ መመዝገብ እንደሚችሉ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ታጋይቱ አባቡ፤ "በአዲስ አበባ ከደረጃ በታች በመሆናቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘ የትምህርት ተቋማት ለቀጣይ ዓመት ወደ ማስተማር ሥራቸው እንዲመለሱ በልዩ ሁኔታ የመመዝገቢያ ቀን ተዘጋጅቶላቸዋል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማቱ እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው በአዲስ እውቅና እንዲመዘገቡ ዕድል እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
"ለትውልድ ግንባታ ጥራት ያለው ትምህርት ወሳኝ ነው፡፡ በጥራት ጉድለት ምክንያት የሚዘጉ ተቋማት መብዛት የሚያስጨንቅ አይደለም" ያሉት ወ/ሮ ታጋይቱ፤ "ከዘርፉ በጥራት ችግር ምክንያት የሚወጡ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ የአዲስ ገቢዎቹ ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ የ2018 ትምህርት ዘመን በአዲሱ ምዝገባ ወደ ትምህርት ዘርፉ ለመቀላቀል ከ300 በላይ ተቋማት መመዝገባቸውንም ምክትል ሥራ አስኪያጇ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ