ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት፣ የነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓትን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀን) በታገዘ ዘመናዊ ስርዓት የመቀየር ሙከራ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ኤጀንሲው ከ14 ዓመታት በፊት የተዘረጋውን የአሰራር ስርዓት ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባከናወነው ሪፎርም፤ በበይነ መረብ (ኦንላይን) መለወጡን የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹሜ አስታውሰዋል፡፡

Post image

በሙከራ ላይ ስለሚገኘው አዲሱ ዘመናዊ የመታወቂያ አሰጣጥ ስርአት ለአሐዱ ሬዲዮ በሰጡት ማብራሪያ፤ "በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) የሚታገዘው አሰራር የሙከራ ጊዜውን ሲያጠናቅቅ ኤጀንሲው የነዋሪነት መታወቂያ፣ የልደት እና ሞት የምስክር-ወረቀቶችን ጨምሮ ሌሎችም የወሳኝ ኩነት ማስረጃዎች ለተገልጋዮች ሲሰጥ በሲስተም መቆራረጥ ምክንያት የሚገጥመውን የደንበኞች መጉላላት ያስቀርለታል፡፡ ለአገልግሎቱ ጥራት መጨመርም የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አክለውም፤ “ከነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ጋር በተያየዘ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን በ'ፎርጅድ' የመሸኛ ደብዳቤ ማጭበርበር ለመከላከል የደብዳቤ ልውውጡን በተቋማቱ መካከል በተዘረጋ የግንኙነት መረብ አማካኝነት እንዲከወን በማድረግ የአጭበርባሪዎችን ተግባር ሙሉ ለሙሉ ለመግታት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በተጭበረበረ ሕገ-ወጥ መረጃ የነዋሪነት መታወቂያ የወሰዱ ጥፋተኞችን ማስረጃዎች ለማጣራትም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት ተቋማት ጋር ውይይት እየተካሄደ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤ.አይ) የታገዘው የነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት የሙከራ ጊዜ ስለሚያበቃበት እና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ስለሚገባት ጊዜ የተባለ ነገር የለም።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ