ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር 5 ወረዳዎች በምዕመናን ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያን የፈፀሙት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መሆናቸውን መረጃ ማገኘቱን አጣሪ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በምስራቅ አርሲ ዞን በምእመናን ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ ግልፅ ማብራሪያ ለመስጠት ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

በዚህም ኮሚቴው ከጥቅም 25 ቀን እስከ 30 2018 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ቀናት በቦታው ተገኝቶ ያሰባሰበውን የመጀመሪያውን ሪፓርተር ዛሬ ሕዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ አደርጓል።

‎በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ ከጥቅምት 12 ጀምሮ በምእመናን ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች የተፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያዎች የመጀመሪያ ዙር ያለውን ሪፖርት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

Post image

በዚህም "አሰቃቂ ግድያውን የፈፀሙት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው" የሚል መረጃ ምግኘቱን፤ በማጣራት ሂደቱ ላይ 'አሰባሰብኩት' ባለው መሠረት አጣሪ ኮሚቴው አስታውቋል።

‎የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ መላዕከ ሠላም ዳዊት ያሬድ እንደገለጹት፤ በዞኑ ስለተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ በቦታው በመገኘት የማጣራት ሂደት ውስጥ የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የተጎጂ ቤተሰብ የዓይን ምስክሮችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና የማህበረሰብ ውይይት ተደርጓል። ‎

በዚህም መሠረት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ የንብረት ውድመት መከሰቱን እንዲሁም፤ እገታ መከሰቱን አረጋግጫለሁ ብሏል።

‎የአጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢው "በጥቅምት 12 ቀን ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ታጣቂ ኃይሎች ማህበረሰቡን አስገድደው ምሳ ከበሉ በኋላ፤ የመንግሥት ኃይሎች መምጣታቸውን ሲያውቁ ሰዎችን አግተው ወደ ጫቃ መሸሻቸውን እና ያገቷቸውን ሰዎች በጥቅምት 14 ቀን እንደገደሏቸው መረጃ አግኝተናል" ብለዋል። ‎

በተለይም ከተጎጂ ቤተሰቦችና ከታጋች ቤተሰቦች በተገኘው መረጃ መሠረት፤ "ግድያውን የፈፀሙት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው" የሚል ምላሽ ተገኝቷል በማለት ኮሚቴው መግለጹን አሐዱ ሬዲዮ ሰምቷል።

‎በአንድ አንድ የአካባቢው ማህበረሰብ በኩል ደግሞ ምንም አይነት ሐይማኖት ተኮር የሌላቸው በሌሊት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንደሆኑ መልስ እንደሰጠው ኮሚቴው አክሎ ገልጿል።

‎ኮሚቴው "በወቅቱ የተገደሉት ዜጎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ብቻ አይደሉም፡፡ ከእስልምና እምነት ተከታዮችም ተገድለዋል" ያለ ሲሆን፤ በመጨረሻው ሪፖርቱ ላይ የአቋም መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ