የሰሜኑ ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም አምስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያው የሰላም ሰምምነት ደግሞ ሦስት ዓመትን ደፍኗል፡፡

ይሁን እንጂ ስምመነቱ ከተፈረመ ከሦሰት ዓመት በኃላም ቢሆን አብዛኛው የስምምነቱ አንቀፆች ያልተፈጸሙ ሲሆን፤ ይህም ለሌላ ዙር ጦርነት እንዳይዳርግ ስጋትን ፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተፈጠረው ውጥረትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደ ይመስላል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት መግታት የቻሉት ሁለቱ ሃይላት ስምምነቱን አጽንተው ዘላቂ ማድረግ ግን ተስኗቸዋል።

በስምምነቱ ማዕቀፍ ውስጥ የተያዙ አንኳር ጉዳዮችን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻላቸውም በመካከላቸው የተፈጠረው መካሰስ እና መወነጃጀል ተባብሷል ቀጥለሏል፡፡ ሌላ ውጥረት እንዳይፈጠርም አስግቷል።

በዚህ ውጥረት መካከል አምስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረውንና የሰሜኑ ጦርነት የተጀመረበትን እና የተሰው ሰማእታትን በተለያየ ሁኔታ የመንግሥት ተቋማት አስበው ውለዋል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ "እንዳይደገም መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ቃል በተከበረው በ5ኛ ዓመት የሰሜን ዕዝ ዝክረ ሰማዕታት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ንግግር አድርገዋል፡፡

Post image

በዚህም "ምንም ብንታገስ ከተጠቃን መከላከላችን አይቀርም" ሲሉ ያደረጉት ንግግር፤ በሁለቱ ሀይላት መካከል ያለውን ውጥረት አጉልቶ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የሰሜኑ ጦርነት የተነሳበትን ሁኔታ ረዘም ላለ ደቂቃ ያብራሩ ሲሆን፤ እንደ ሀገር መከዳት እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሁልጊዜም ለሰላማዊ መንገድ በሩን ክፍት ማድረጉን ጠቁመው፤ "ከትላንት ባለመማር የሚደረግ ፉከራ መቆም አለበት" ሲሉ አስጠንቀቀዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት የቆመ ለሰላም ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፤ "መከለከያ ሠራዊት ፓርቲ አይደለም ተወዳድሮ ስልጣን አይዝም" ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በሚጠበቀው መልኩ ሙሉ ሙሉ አለመተግበሩ በተለይም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸው ለዳግም አለመግባባቱ እንደምክያት ይጠቀሳል፡፡

በተጨማሪም ህወሓት ሠራዊት እያሰለጠነና እያስመረቀ መሆኑም ስምምነቱን የሚጥስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጭምር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

አሁን ላይ 'በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ መፍታት ካስፈለገ መፍትሄው ምን ይሆን?' የሚለው የብዙሀኑ ጥያቄ ነው ሲሉ የተናገሩት፤ ጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡

Post image

ሊቀመንበሩ ሀሳባቸውን ሲገልፁ ወታደራዊ ርምጃ ተገቢ አለመሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፤ ሕግ የማስከበር ዘመቻ አሁንም እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን "ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ አያመጣም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"የፖለቲካን አደገኝነት መረዳት ያስፈልጋል" የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ በጉልበት መፍትሄ ይመጣል ተብሎ መታመን የለበትም ሲሉም አክለዋል፡፡

በመሆኑም በትግራይ ክልል ያለውን አሁናዊ ሁኔታ መፍታት ካስፈለገ፤ ሁሉንም ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊወሰድ እንደሚገባ አቶ ዘሪሁን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

"ጉዳዩ በሽምግልናም ሆነ በሌላ መንገድ አይፈታም" የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ አካታች የሆነ ውይይት መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ስምምነቱ ቀድሞውንም ግልፅነት ሊኖረው ይገባ ነበር" ያሉም ሲሆን፤ ይህንን ለመፍታት ከብሽሽቅ ፖለቲካ መውጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በትላትናው ዕለት በነበረው የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ፤ ያለፈውን ጦርነት ምክንያት ብቻም ሳይሆን አሁን ስላለው ውጥረትም ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸውም "የባንዳ ሥራ ላይ የተሰማሩና ሕዝቡን የማይወክሉ" ያሏቸው ኃይሎች፤ ከሀገር ክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከዚሕ በተጨማሪም "ጦርነት አንፈልግም" ያሉ ሲሆን፤ "በልማታችን ላይ የመጣውን ግን መመከት አለብን የታጠቅነውም ለዚህ ነው" ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡

Post image

በንግግራቸው የህወሓት አካላት አሁን ላይ እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ማሳሳቢያ የሰጡ ሲሆን፤ "ከተጠቃን እራሳችንን እንከላከለን" ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህ የኢታማዦር ሹሙ ንግግር ለህወሓት ቀጥተኛ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን ስጋትንም መፍጠሩ ይነሳል፡፡

ይህንን በሚመለከት ያነጋገራናቸው የትንሳኤ ስርዓት የቃንጪ ሓቂ ፓርቲ ሊቀመንበር ደጋፊ ጎደፋይ፤ ጦርነት መፍትሄ አይሆንም ይላሉ፡፡

"እንደ ሀገርም እንደ ዓለም የጦርነትን አስከፊነት ተመልክተናል" ያሉት ሊቀመንበሩ፤ መፍትሄው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈፀም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በዋናነትም በክልሉ ያለው ጊዚያዊ አስተዳደር አካታች ባለመሆኑ ችግሮች መኖራቸውን በማንሳት፤ አሁንም ሁሉን ያቀፈ አስተዳዳር መቋቋም አለበት ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል በቀጠለው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹም ሲሆን፤ በተለይም ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር የፈጠረው ጥምረት ከፌደራል መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ እንዳይከት እያሳቡ ይገኛሉ፡፡

አሁን እየተካሄዱ ያሉ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችም 'ሌላ ዙር ጦርነት ዝግጅት እየተደረገ ነው' የሚሉ ሀሳቦች እየተነሱ ሲሆን፤ ጦርነቱ የማይቀር ከሆነ እንኳን ሕዝብ ሊጠበቅ ይገባል የሚሉ ድምፅችም መሰማት ቀጥለዋል፡፡

በርካቶች አሁን ህወሓት ላገኘው ከፍተኛ ስልጣን ተጠያቂ የሚያደረጉት የፌደራል መንግሥቱን ሲሆን፤ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉለሙሉ ማስከበር ቢችል ኖሮ ችግሮች መቀረፍ ይችሉ እንደነበር ያነሳሉ፡፡

የፌደራል መንግሥቱ በአንጻሩ "የፕሪቶሪያው ስምምነት ህወሓት መሳሪያ ሊያስረክብ ይገባል ይላል እንጂ፤ መሳሪያ ይደብቅ አይልም፤ ወታደርም እያሰለጠነ ያስመርቅ አይልም" ሲል ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡

እነዚህና መሰል እሰጥ አገባዎችን ለመፍታት በትግራይ ሁሉንም አካታች የሆነ አስተዳደር መፍጠር ካልተቻለና ስምምነቱ መተግባር ካልቻለ፤ ለግጭት መንስኤ ይሆናል ያሉት ደግሞ፤ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ዋና ሊቀመንበር ደጀን መዘገቦም (ዶ/ር) ናቸው፡፡

Post image

በትግራይ ክልል ያለው የውስጥ ውጥረት እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ጋር እየተፈጠረ ያለው መካሳሰስ ውጥረቱን እያባባሰው እየሄደ ነው፡፡

በተጨማሪም ፌደራል መንግሥት ከኤርትራ መንግስት ጋርም በተመሳሳይ መካረር ውስጥ መግባቱ ቀጠናውን የጦርነት ደመና ከወረረው ሰንብቷል፡፡

ይህ ደግሞ 'ኢትዮጵያ ካልተወጣችው የጦርነት አዙሪት ዳግም የሚከታት ሊሆን ይችላል' የሚለው የብዙዎች ስጋት መሆኑን መመልከት ያስችላል፡፡

አቶ ብርሀነ አፅብሃ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፤ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት በቅድሚያ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈፀም አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Post image

ይህ ከሆነ በትግራይ ላይ ያንዣበበውን ጦርነት ሕዝቡ ሊያከሽፈው ይችላል የሚል ዕምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያሉ አመራሮችም ሆነ የፌደራል መንግሥት በክልሉ ያለውን ውጥረት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ይሁን እንጂ በትላትናው የሰሜኑ ጦርነት አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ጠቅላይ የኢታማዦር ሹም የሰጡት ሀሳብ የነገሮችን ባሉበት መቀጠል ያመላከተ ሆኗል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ