ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአማራ ክልል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየ ያለው አለመረጋጋት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ሲል የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በኮሚሽኑ የሚዲያ ክፍል ዋና ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ፤ በተለይም የምስራቅ እና የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ለሕገ-ወጥ ስደት እንደ መውጫ በር ከሚያገለግሉት መካከል ዋነኛዎቹ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ምክንያት በቂ የሥራ ዕድል አለመፈጠሩ በርካታ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ እንዲሰደዱ ማድረጉን ያነሱም ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ዜጎች ለከፍተኛ ስቃይ እና መጉላላት እየተዳረጉ መሆኑን አስረድተዋል

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎች ድንበር አቋርጠው ለመሰደድ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓዙ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪነት ጋር የተያያዘ ሥራ ሲሰሩ የተገኙ 126 ደላሎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህንንም የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ