ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት 900 ቢሊየን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ለምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ተናግረዋል፡፡
በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት አጠቃላይ ወጪ 1 ነጥብ 2 ትሪልዮን ብር እንደሆነና የ300 ቢልዮን ብር ልዩነት እንዳለው፤ ይህም ከግብር የተገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።
"46 ሺሕ የሚሆኑ የታክስ ተመዝጋቢዎች ግብር አይከፍሉም ምክንያቱ ደግሞ ግማሹ ሰረቼ ከሰርኩ የሚል ሪፖርት ያቀርባል፤ ገቢና ወጪው ተመጣጣኝ አይደለም እንዲሁም ሪፖርት የማያቀርቡ አሉ" ብለዋል።
"በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ፈቃድ ከወሰዱት መካከል ግብር እየከፈሉ ያሉት 37 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
"37 የሚሆነውን ግብር ከፋይ 50 በመቶ ብናደርሰው ዘንድሮ የሰበሰብነው ገቢ በከፍተኛ ጀረዳ ይጨምራል" ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
አክለውም፤ የግብር አከፋፈልን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ቢሆንም፤ የታክስ አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 5 ለሚልዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ አጥነትን ይቀላቀላሉ" በማለት ጥያቄያቸውን ላቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አበባው ደሳለው በሰጡት ምላሽ ነው፡፡
የምክር ቤት አባሉ፤ "በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፤ አሁን በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ አጥነትን ይቀላቀላሉ፤ ይህን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው?" የሚል ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅርበዋል፡፡
"በ2017 ዓ.ም. 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል" የሚል ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት ሰዎች በግብርና ዘርፍ፣ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በአገልግሎት ዘርፍ፣ ከ680 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በኢንዱስትሪ እንዲሁም የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ከ500 ሺሕ በላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ሌሎች ያልተጠቀሱ ዘርፎችን ጨምሮ በድምሩ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም፤ "ከወጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ከዚህ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በ2017 በጀት ዓመት የተገኘው ገቢ ከወጪው ጋር ሲቀናነስ የ300 ቢልዮን ብር ልዩነት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ
በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 5 ለሚልዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል
