ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል አሁን ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ ሥራዬ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አድርጎብኛል ሲል አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ፤ በክልሉ ሀገራዊ ምክክር ለማስጀመር እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር ውይይት ሲያድረግ መቆየቱን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይና የዋና ኮሚሽነሩ ልዩ አማካሪ አቶ ጥበቡ ታደሠ፤ በክልሉ ምክክር ለማድረግ ግልፅ ደብዳቤ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመላክ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ "ይህ ጥሪ በተጋጋሚ ጊዜ ሲደረግ ቆይቷል" ብለዋል።

"በትግራይ ክልል ለሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና ምሁራን ጋር ውይይት ተካሂዷል" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የሀገራዊ ምክክሩ በትግራይ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ላይ መወያየታቸውንም ገልጸዋል።

"ይሁን እንጂ በክልሉ እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አጀንዳ ማሰባሰብ የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለንም" ሲሉ አቶ ጥበቡ ታደሠ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ይህም በኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልጸው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት እና ሌሎችም ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላው ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታች እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ገልጿል።

በተለይም ከምክክሩ የወጡና ያልገቡ ፖርቲዎች እንዲሁም ታጣቂዎች ወደ ምክክር ሂደቱ እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብሏል።

ከምክክሩ ካቋረጡ ፖርቲዎቸ ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ሂደቱ እንዲመለሱ ከሦስት ፖርቲዎች ማለትም እናት ፖርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ (ኢህአፓ) ጋር ተወያየተዉ እንዲመለሱ እየተሰራ ስለመሆኑም አስታውቋል።

"እስካሁን ያልተሳተፉ ፖርቲዎች ኮከስ መስረተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው" ያሉት የምክክር ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ፤ "ወደ ምክክር እንዲመጡ ለማረድረግ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

"ይሁን እንጂ የኮከሱ አባላት የሆኑ ፖርቲዎች ምንም አይነት ፍቃደኝነት ሊታይ አልቻለም" ሲሉም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ታጣቂዎች ወደ ምክክር እንዲመጡ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ እስካሁን በግልፅ ፍቃደኝነት እየታየ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"በዚህም ምክንያት የምክክሩ ሥራን ወደ ኃላ የሚጎትት ሁኔታን እየተፈጠረ ይገኛል" ሲሉ ገልጸዋል።

አሁንም ኮሚሽኑ ወደ ምክክር እንዲመጡ ለታጣቂዎችም ጥሪ ያቀርባል ተብሏል።

ኮሚሽኑ ከዚህ በኃላ በተከታታይ በየ15 ቀኑ መግለጫ መስጠት ይቀጥላል ሲሉም የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ