ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካ ወታደሮች ከአራት ዓመታት በፊት ሀገሪቱን ለቀው በወጡበት ወቅት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረው የታሊባን ባለስልጣናት ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት በሚደረገው ጥረት ሩሲያ የአዲሱን የአፍጋኒስታን አምባሳደር የሹመት ደብዳቤ ተቀብላለች።
"የአፍጋኒስታን እስላማዊ ኢሚሬትስ መንግስት ይፋዊ እውቅና የመስጠቱ ተግባር በሀገሮቻችን መካከል በተለያዩ መስኮች ውጤታማ የሁለትዮሽ ትብብር እንዲጎለብት ያደርጋል ብለን እናምናለን" ሲል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒቴሩ በመግለጫው "ከአፍጋኒስታን ጋር በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በግብርናና መሠረተ ልማት መስኮች ላይ የንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር ማድረግ የሚቻልበት ዕድልን እየተመለከተች ነው" ሲል ገልጿል።
እንዲሁም ሞስኮ ቀጣናዊ ፀጥታን በማጠናከር እንዲሁም ሽብርተኝነትን እና ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በመዋጋት ረገድ የካቡል መንግሥትን መርዳቷን እንደምትቀጥል አመላክቷል፡፡
ይህም እርምጃ ሩሲያ በዓለም ላይ የሀገሪቱን የታሊባን መንግሥት እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር አድርጓታል።
የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ በአፍጋኒስታን የሩሲያ አምባሳደር ከሆኑት ዲሚትሪ ዝሃሮኖፍ ጋር በትናንትናው ዕለት በካቡል ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ፤ "ይህ ደፋር ውሳኔ ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

"አሁን እውቅና የመስጠት ሂደት ተጀምሯል ሩሲያ ከሁሉም ቀድማለች" ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ የሩሲያ እርምጃ ዋሽንግተን በአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲታገድ እና በታሊባን ውስጥ ባሉ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያሳለፈችውን ውሳኔ በቅርብ እንድከታተለው የሚደረግ ነው ሲል አልጀዚራ በዘገባው አመላክቷል፡፡
የዋሽንግተን ማዕቀብ የአፍጋኒስታን የባንክ ዘርፍ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥ አስተዋጽኦ ማድረጉ ሲገለጽ ቆይቷል።

የታሊባን መንግሥት እ.ኤ.አ በነሀሴ 2021 የአሜሪካ ኃይሎች አፍጋኒስታንን ለቀው በወጡበት ወቅት፤ ስልጣኑን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ታሊባን ሥልጣን ሲቆጣጠር በአፍጋኒስታን ኤምባሲያቸውን ካልዘጉ ጥቂት አገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ሆና ቆይታለች።
የአሜሪካን መውጣት "ውድቀት" ስትል የምትጠራው ሞስኮ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከታሊባን ባለስልጣናት ጋር ያላትን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ እርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን፤ "ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አቅም ያለው የኢኮኖሚ አጋር" ስትልም ታሊባንን ትገልጻች፡፡
የታሊባን የልዑካን ቡድን እ.ኤ.አ በ2022 እና 2024 በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ ዋና የኢኮኖሚ መድረክ ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ የቡድኑ ከፍተኛ ዲፕሎማት ባለፈው ጥቅምት ወር ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተገናኝቷል።
በተጨማሪም በሃምሌ ወር 2024 ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ታሊባን ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አጋር" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታሊባን ከሩሲያ የአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ የሰረዘ ሲሆን፤ ይህ የሆነው ከካቡል መንግሥት ጋር የተሟላ ትብብርን ለመፍጠር እንደሆነ ሩሲያ አስታውቃለች።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ