ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት በቅርቡ በጂዳ ከተማ 'አንድ ህንዳዊ ዜጋ ላይ ተኩስ ከፍተው ገድለዋል' ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የጂዳ ግዛት ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፤ የሀገሪቱን የድንበር ደህንነት ደንቦች በመጣስ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚኖሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
በከተማዋ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ሕገ-ወጥ ዕፅ በመገበያያት ላይ በነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ጠብና አለመግባባት ሳቢያ ህንዳዊው ግለሰብ በጥይት መመታቱን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በዚህም በግጭቱ ወቅት ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ ኢትዮጵያዊ በህንዳዊው ተጎጂ ላይ ተኩስ ከፍቶ ጉዳት እንዳደረሰበት የገለጸው ፖሊስ፤ በጥይት የተመታው ግለሰብ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ቢወሰድም፣ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉን አስታውቋል፡፡
በዚህ ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ የተመሰረተባቸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በአካባቢው በዕፅ እና በኮንትሮባንድ ዝውውር ውስጥ ተሰማርተው እንደነበት የገለጸው የከተማዋ ፖሊስ፤ በተጨማሪም የድንበር ደህንነት ደንቦችን በመተላለፍ ተይዘው ለተጨማሪ ሕጋዊ ሂደት ወደ ዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውን ገልጿል።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጪ ሀገር ዜጎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም ክስተት በሀገሪቱ በድንበር ጥሰትና በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ ከሚወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ