ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጀማሪ ተማሪዎችን ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ የፋይዳ መታወቂያ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ተከትሎ፤ በሲስተም መዘግየት ምክንያት የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በፍጥነት ማግኘት ባለመቻላቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ማስመዝገብ እንዳልቻሉና ለእንግልት እንደተዳረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል።

በ2018 ዓ.ም. የፋይዳ እና የልደት ካርድ ሕጻናት ተማሪዎችን ለትምህርት ቤት ለማስመዝገብ በቅድመ ሁኔታነት መቀመጡን ያስታወሱት ወላጆች፤ የትምህርት ምዝገባው ከመጀመሩ በፊት የፋይዳ ምዝገባ ማዕከላት በመሄድ የልጆቻቸውን የጣት አሻራ ያስመዘገቡ ቢሆንም እስካሁን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

Post image

በዚህም፤ "መታወቂያው በጊዜ ባለመድረሱ ምክንያት የምዝገባ ቀኑ ያልፋል የሚል ስጋት ውስጥ ወድቀናል" ብለዋል።

አሐዱ የነዋሪዎች ቅሬታ ተቀብሎ የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራምን ጠይቋል።

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ፤ ችግሩ የተፈጠረው የሲስተም መጨናነቅ በፈጠረው የተመዝጋቢ ብዛት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ከፍተኛ የምዝገባ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የፋይዳ ሲስተም አንድን ሰው በልዩ ሁኔታ ለማጣራት የሚወስድበት የጊዜ ልኬት በጥቂቱ እንዲጨምር ማድረጉንም አስረድተዋል።

"በሲስተም መጨናነቁ ምክንያትም አንድ ተመዝጋቢ የመታወቂያ ቁጥሩን ለማግኘት እስከ 1 ሳምንት ሊጠብቅ ይችላል" ያሉት አስተባባሪው፤ አብዛኛው ወላጅ ቀድሞ ባለመዘጋጀቱ መጨናነቅ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ይህ መጨናነቅም በዚህ እንደማይቀጥል አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ300 በላይ የፋይዳ መታወቂያ የመመዝገቢያ ቦታዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ አገልግሎቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 19 ሚልዮን ሰዎች መታወቂያ አግኝተዋል ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ