ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ያለው የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ዋጋ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ያማከለ እንዲሆን መንግሥት ለቤት ገንቢዎች እና ለቤት ፈላጊዎች በፖሊሲ የታገዘ ድጋፍ ማድረግ አለበት ሲሉ፤ አሐዱ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚክስ እና ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

"በአዲስ አበባ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ የገዢዎችን አቅም ያገናዘበ አይደለም" የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ "የገንቢዎች ቁጥር እና የግንባታው መጠን ቢጨምርም የቤት ዋጋ ያልቀነሰው፤ አብዛኛው ቤት መገንቢያ ግብዓት ከውጭ ሀገር በዶላር ተገዝቶ የሚገባ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ተመራማሪ ዘነበች አድማሱ (ዶ/ር)፤ "የመኖሪያ ቤት ገንቢዎችም ሆኑ መንግሥት በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ጥረት ማድረግ አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ተመራማሪዋ ሀሳባቸውን ሲያብራሩ፤ "መንግሥት የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸት፣ የግንባታ ቦታን በቅናሽ እና ባልተራዘመ ቢሮክራሲ ማቅረብ፣ የግንባታ ግብአቶች ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማበረታታት ይጠበቅበታል" ብለዋል።

Post image

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶ/ር ቆስጠንጢንዮስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፤ "የመኖሪያ ቤቶችን በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ ካልተቻለ የቤት አቅርቦት ችግርን መፍታት አይቻልም" ብለዋል። የግንባታ ግብዓቶችን ከማምረት በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሙያ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም መክረዋል።

በተጨማሪም መንግሥት የመጀመሪያ ቤት ገዢዎችን ቀረጥ በመቀነስ፣ ለግንባታው ወጪ የሚቀንሱ ፖሊሲዎችን አስገዳጅ በማድረግ፣ በሽያጭ ላይ ያለውን የደላላ ጣልቃ-ገብነት በማጥፋት እና ይህንን መሰል ፖሊሲዎችን በመከተል የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ዋጋ እንዲቀንስ ማድረግ ይገባዋል ተብሏል።

በቅርብ ጊዜ ይፋ የተደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢትዮጵያን ዜጎች በቀላሉ ቤት መግዛት ከማይችሉባቸው ሀገራት መካከል ከመጨረሻዎቹ ተርታ አስቀምጧታል።

ኑምቤዮ የተሰኘው ተቋም ይፋ ባደረገውና 104 ሀገራትን ባካተተው ጥናት፤ ኢትዮጵያ ኩባን እና ሶሪያን ቀድማ ከመጨረሻ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

እንደ ጥናቱ ማብራሪያ አንድ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ቤት ለመግዛት ለ47 ዓመታት ሙሉ ገቢውን መቆጠብ አለበት። ይህ አሃዝ ወደ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲወርድ ወደ 56 ዓመት ከፍ ያላል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ