ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሊባኖስ በተለያየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 28 ዜጎች (26 አዋቂዎችና ሁለት ሕጻናት) በቤይሩት-ሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤት እና በተባባሪነት ባለድርሻ አካላት ትብብር ወደ አገራቸው እንዲሳፈሩ መደረጉ ተገልጿል።
ወደ ሀገር እንዲመለሱ የተደረጉት በሊባኖስ በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ የቆዩና በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር እና እንግልት ተጋልጠው ወደ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ በመምጣት በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒት ማህበር ጊዜያዊ መጠለያ አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ 24 ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እንዲሁም፤ በካሪታስ መጠለያ የነበሩ 2 ዜጎች ከእነ ልጆቻቸው መሆናቸውን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ዜጎቹ ELMA Foundation፣ Freedom Fund Ethiopia እና Arcenciel Lebanon ከተሰኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጉዳያቸው በቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ በኩል አልቆላቸው፤ ትናንት ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው እንዲሳፈሩ መደረጉ ተገልጿል።
ዜጎቹ ኢትዮጵያ ሲደርሱም አቀባበል ተደርላቸው ወደ ጊዜያዊ መጠለያ በመግባት፤ የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተመላክቷል።
ከመጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ በተጀመረው 4ኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለስ ሥራ መሠረት፤ እስካሁን ለ54 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር መመለስ መቻሉን የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 28 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲሳፈሩ መደረጉ ተገለጸ
