ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በተከሰተ ጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው እንዲሁም፤ ወደ ትምህርት ቤት መላክ የሚገባቸው ሕጻናት ቤት መዋላቸው በሀገር ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በፊት በአስቸኳይ እልባት እንዲበጅለት አሐዱ ሬዲዮ ያነጋገራቸው መምህራን አሳስበዋል።

መምህራኑ፤ "በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ያደረገው ተራዛሚ ግጭት በፍጥነት ካልተቋጨ እና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ካልተገባ፤ ዕውቀት እና ክህሎት መቅሰሚያ ጊዜውን ያባከነ ወጣት ቁጥር ሀገር ከምትሸከመው በላይ የመሆን እድሉ በእጅጉ ይሰፋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ለአሐዱ ሐሳባቸውን ከሰጡ መምህራን መካከል የሆኑት መምህር ትሁት ተገኑ፤ "ሀገር ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንድታስመዘግብና የዜጎቿ ኑሮ እንዲሻሻል ትምህርት ወሳኝ ነው። ለውጥ ለሚያመጣ የመማር ማስተማር ሂደት ደግሞ ሰላም መሰረታዊ ነው" ብለዋል።

የተማረ ዜጋ ቁጥር መጨመር ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አንስተው፤ "በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈታ የሚችልን አለመግባባት በጠመንጃ አፈ-ሙዝ መካሄዱ የትምህርት ስርአቱን ጎድቷል፤ የዚህ ኪሳራ ደግሞ በልጆቻችን ብቻ ሳይሆን በሐገራችን የነገ ተስፋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው" የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የቀደመውን ሐሳብ የሚጋሩት መምህር በለጠ አይዛ በበኩላቸው፤ "ትምህርት ማኅበረሰቡ ለረዥም ዘመናት ያከማቸውን ጥበብና ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍበትና ወጣቱን ለቀጣይ ማኅበራዊ ሕይወት የማዘጋጀት ቁልፍ ሚና ቢኖረውም፤ ለተራዘመ ዓመት በግጭትና ጦርነት መፈተኑ ከፍተኛ ስጋት ያጭራል" ብለዋል።

"ለዘርፉ ማነቆ የሆነውን የሰላም እጦት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን መርህ የሚያደርጉ መልካም ዜጎችን ማፍራት፣ ኢትዮጵያን ትልቅ ሀገር ለማድረግ ተቀዳሚ መንገድ ነው" ያሉት መምህር በለጠ፤ "አሁን ያለው የተራዘመ ግጭት ያልተማረውን የሰው ኃይል ያበዛል፣ ትውልድን በዕውቀት ያቀጭጫል" ሲሉ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በ2014 ዓ.ም. ብቻ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያት ከ3 ነጥብ 2 ሚልዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል።

ዩኒሴፍ ባወጣው ሪፖርት ደግሞ በ2017 ዓ.ም. ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕፃናት በትምህርት ገበታ ላይ እንዳልተገኙ አመልክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ