ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን የሚመለከት አጠቃላይ ሀገራዊ መረጃ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡

ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ከዋነኛ ምክንያቶቹ መካከል ደግሞ የተፈጸሙት ጥቃቶች በበቂ ሁኔታ ሪፓርት ያለመደረጋቸው መሆኑ ይገለጻል፡፡

የመረጃ አሰባሰበና አስተዳደር ደካማ መሆን በሀገሪቱ እየተፈፀመ ያለውን ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መጠን የሚያሳይ ወቅታዊ እና ደረጃውን የጠበቀ መረጃ፣ ጥናትና የምርምር ሥራ አለመኖር ይገኙበታል፡፡

ነገር ግን በ2008 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብና ጤና ጥናት እና በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የተከናወኑ ሌሎች ጥናቶች ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት እንደሚፈፀምና የዚህ ድርጊት ዋና ሰለባዎች ሴቶችና ልጃገረዶች እንደሆኑ ያሳያል፡፡

Post image

ጥናቱ እንደሚያረጋግጠው ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሆኑ ሴቶች መካከል 23 በመቶ አካላዊ ጥቃት ሲደርሰባቸው፤ 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ነፍሰ ጡር ከሆኑ ሴቶች መካከል 4 በመቶ አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸውም ታውቋል።

ትዳር ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች መካከል 34 በመቶ ያህሉ አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስነ-ልቦናዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡

በዚህ ረገድ ያለው አሐዝ በኦሮሚያ 38 በመቶ፣ ሀረሪና አማራ 35 በመቶ፣ ትግራይ 32 በመቶ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 32 በመቶ፣ በቀድሞ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች 29 በመቶ፣ አዲስ አበባ 26 በመቶ እና ሶማሌ ክልል 9 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

የ2008 ዓ.ም ጥናት ፆታን መሠረት በማድረግ የሚፈፀሙት ጥቃቶች ባህሪያት እና ምክንያቶቻቸው ሥር ከሰደዱ ማህበረሰባዊ እሴቶች፣ ልምዶችና ተግባራት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ጤና ጥናት እንደሚያሳየው ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 49 ከሆኑ ሴቶች መካከል 23 ነጥብ 6 በመቶ እንዲሁም ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 59 መካከል ከሆኑ ወንዶች ደግሞ 16 ነጥብ 8 በመቶ የሴት ልጅ ግርዛት ሐይማኖታዊ ድጋፍ ያለው ነው ብለው ያምናሉ፡፡

Post image

የኢትዮጵያ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ዙሪያ ከሰሞኑ ውይይት ያደረገበት ሲሆን፤ በርካታ ሀሳቦችም ተነስተዋል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ እንደ ሀገር የልጅነት ጋብቻም ሆነ ጎጂ ልማዳዊ ድርጆቶች በስፋት የሚስተዋልበት ሁኔታ መቀነስ ማሳየቱን ይናገራሉ፡፡

ይሁን አሁንም ያለዕድሜ ጋብቻ የመሰሉ ድርጊቶች እየተፈፀሙ መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን ወደ 42 በመቶ በሀገሪቱ ይህ ድርጊት ይፈፀማል ይላሉ፡፡

የልጅነት ጋብቻን እያባባሰ ያለው ጥሎሽ ነው የሚሊት ኃላፊው ለአንድ ልጃገረድ ሴት እስከ 20 ከብት ድረስ ይቀርባል ብለዋል፡፡

ይህ ሁኔታ የልጅነት ጋብቻን ከፍ ሊያደርገው መቻሉን የገለፁ ሲሆን፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል እርዳታ የሚሹት አንድ አራተኛዎቹ ብቻ መሆናቸው መረጃዎች ያሰረዳል፡፡

አብዛኞቹ 34 በመቶ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እርዳታ የሚሹት ከጎረቤቶቻቸው ሲሆን፤ ከሕግ ባለሙያዎች፣ ከሐኪሞች ወይም ከሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት እርዳታ የሚጠይቁት 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውም ይገለጻል፡፡

ይህንን በሴቶች ላይ የሚደረስ ፃታዊ እና አካላዊ ጥቃቶችን ለመፍታት በተለይም የሕግ አፈፃፀሙ ላይ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ አቶ ዘካሪያስ ይናገራሉ፡፡

Post image

ከጥቃቶች በተጨማሪ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ችግሮችን ከፍ ያደረገው የማህበረሰብ ተቀባይነት ማግኘቱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ሰብአዊ መብቶች የማይነጣጣሉ አንዱ ከአንዱ ጋር የተያያዙና የተዛመዱ የሰው ልጆች በተፈጥሮ ያገኟቸው መብቶችና ለሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር እኩል ጠቃሚ የሆኑ መብቶች ናቸው፡፡

አሁን በማሻሻል ያለው የሴቶች ማብቃትና የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ፖሊሲ ካስቀመጣቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱም በሴቶች እና ሕጻናት ደህንነት ላይ ጉዳት የሚያደረሱትን ጎጂ የሆኑ ድርጊቶችን ማስወገድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል እንዲሆኑ በማወጅም በሴቶች ላይ የሚደረሰውን ማንኛውንም አድልዎ ለማስወገድ የወጣ ስምምነት እና ቃል-ኪዳኖችን ተፈፃሚ ማድረግ እንደሚገባ ይነሳል፡፡

Post image

ይህንን በሚመለከት የሚገልፁት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ፤ በዚህ ዙሪያ ፍርድ ቤቶች ሆኑ ሁሉም የፍትህ አካላት አስተማሪ የሆነ የሕግ ማሻሻያ ማድርግ ይገባቸዋል፡፡

ያሉት ሕጎችም በትክክል አስተማሪና ድርጊቱ እንዳይደገም የሚያደርጉ መሆናቸውን መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የግንዛቤ እጥረት በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለው የግንዛቤ ማነስ፣ በወንዶችና ሴቶች መካከል ስር የሰደደ ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት መኖር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ እንዲቀጥሉ ፍላጎት ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡

ሌላው ድህነት እና የኢኮኖሚ ልዩነት- በማሕበረሰቡ ውስጥ ሴቶችና ሕጻናት ባላቸው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑና ስለመብቶቻቸው ለመደራደር ያላቸው አቅም አነስተኛ እንዲሆን በማድረጉ ድርጊቶቹ ለማስወገድ ተግዳሮት መሆኑም ይነሳል፡፡

አቶ ዘካሪያስ ከፈፃሚ አካላት ጋር በጋር የሚሰራው ሥራ አንዱ በሌላው ላይ ጣቃ የመግባት ሳይሆን፤ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት ያስበ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በዋናነትም ይህ ስምምነቱ በተለይም ከሕግ አካላት ጋር ክፍተት መኖሩ በመገንዘብ በጋራ በመስራት ችግሮችን መለየት እና አጥቂዎች ትክክለኛ ፍርድ የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ዕምነት እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡

ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የአካል፣ የወሲባዊና የስነ-ልቦናዊ፣ የኢኮኖሚ ጭቆናና ብዝበዛንም ያካትታል፡፡

Post image

በተለይ ወሲባዊ ጥቃት የትኛውንም አይነት ወሲባዊ ድርጊት ከአንድ ሰው ፍላጎት በተፃራሪ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚፈጸም በርካታ ፀያፍ ድርጊቶችን የሚያካትት ነው፡፡

ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን በተመለከተ የተጠቀለለና ወጥ የሆነ ሕግና የአሰራር ስርዓቶች አለመዘርጋት ደግሞ፤ አንዱ ተግዳሮት መሆኑ ይነሳል፡፡

በተጨማሪም ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን የሚመለከቱ ሥራዎች የሚመሩባቸው ግልፅና መሰረታዊ መርሆች በማስቀመጥ ረገድ ክፍተት መኖሩ ይነሳል፡፡

በመሆኑም የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶች ከሰብዓዊ መብት፣ ከማህበረሰብ ጤና፣ ከእድገትና ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በጥብቅ የሚተሳሰሩ ጉዳዮች በመሆቸው ሁሉም አካላት በትብብር እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ