ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር የሩዋንዳ አማፂያን እጃቸውን ይስጡ ሲል ጥሪ አቀረበ
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር አማፂያኖቹ በሰላማዊ መንገድ እጃቸዉን በመስጠት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ጠይቆ፤ እምቢ ካሉ ግን በግዳጅ ትጥቅ ለማስፈታት፤ ወታደራዊ ጥቃቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።
እንደ ኮንጎ ጦር መግለጫ ከሆነ፤ የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዲሞክራሲያዊ ሃይል (ኤፍ.ዲ.ኤል.አር) አማፂያን በሀገሪቱ ያለውን ሁከት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ትጥቅ ፈትተው እጃቸውን እንዲሰጡ አዝዟል።
አማፂያኖቹ ወደ መጡበት ወይም ወደ ሩዋንዳ እስኪመለሱ ድረስ ለመንግሥት ባለስልጣናት ወይም በኮንጎ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ (MONUSCO) እጃቸውን እንዲሰጡ ጦሩ መመሪያ ሰጥቷል።
ነገር ግን አማፂያኖቹ ትጥቅ ለመፍታት ፍቃደኛ ሳይሆኑ እምቢተኛነታቸውን ለማስቀጠል ከሞከሩ፤ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ አደራዳሪነት በተደረገው ስምምነት መሰረት ትጥቃቸውን ለማስፈታት የሃይል እርምጃ ጭምር እንደሚወስድ የኮንጎ ጦር አስታውቋል።
እንዲሁም የፖል ካጋሚ አስተዳደር ታጣቂዎቹን ከኮንጎ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲስወጣ ሲል ጦሩ ጠይቋል።
የሩዋንዳ መንግሥት ከኮንጎ ጦር የቀረበበትን ክስ ምንም አይነት ማስተባበያ ሳይሰጥ ያለፈ ሲሆን፤ ነገር ግን እራሱን የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዲሞክራሲያዊ ሃይል (ኤፍ.ዲ.ኤል.አር) የሚባለውን አማፂያን በአሸባሪነት ከፈረጀው ዓመታትን ተቆጥረዋል።
የሱዳን ጦር በሰው አልባ አውሮፕላን 16 ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉ ተገለጸ
በሰሜን ዳርፉር በኤል ፋሸር በምስራቅ አል ኩማ በተባለች ከተማ የሱዳን ጦር በፈጸመው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ 16 ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ አስተዳዳሪዎች አስታውቀዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን፤ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ተቆጣጥረዋት በምትገኘው ኤልፋሸር ከተማ ነዉ።
በዚህም የሱዳን ጦር ከተማዋን ለመቆጣጠር በከፈተው ጥቃት የ16 ንፁሃን ሰዎችን በሰዉ አልባ ጥቃት ገድሏል ነው የተባለው።
ጦሩ በግዛቲቱ ላይ ከ150 በላይ የአየር ጥቃት ፈፅሞ ንፁሃን ሰዎች ከመግደል በተጨማሪ፤ እንደ ዉሃ፣ መብራትና መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን በመግለጽ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ክስ አቅርበዋል።
አንድ የአካባቢው አስተዳዳሪ ስለ ጥቃቱ በግል የማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት ቪድዮ መልዕክት፤ የሰው አልባ ጥቃቱ የተፈፀመው ማህበረሰቡ በወቅታዊ አካባቢያው ጉዳይ ላይ በተሰበሰቡበት ነው ሲሉ ክስ አቅርበዉ፤ በዛ አካባቢ ደግሞ ታጣቂ ሃይሎች የሉም ሲሉ መግለጻቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
ነገር ግን ክስ የቀረበባቸውና በታጣቂ ሃይል ግማሽ ግዛቶቻቸውን ተነጥቀው፤ ዋና መቀመጫቸውን ከአንዴም ሁለቴም እየተነጠቁ ቦታ በመቀያየር ላይ የሚገኙት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል አልቦረሃን ጉዳዩን አስመልከተው የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
የአፍጋኒስታኑ ታሊባን ወታደራዊ መንግሥት 58 የፓኪስታን ወታደሮችን መግደሉን አስታወቀ
የታሊባን መንግሥት በሰሜናዊ ድንበር ላይ በሚገኙ በርካታ ተራራማ ቦታዎች የፓኪስታን ወታደሮች ላይ በትላንትናው ዕለት በከፈተው ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ፤ 58 የፓኪስታን ወታደሮችን መግደሉን አስታውቋል፡፡
የታሊባን መንግሥት ቃል አቀባይ ዘቢሁላህ ሙጃሂድ፤ ኦፕሬሽኑ በተለያዩ የድንበር ኬላዎች ላይ መደረጉን ገልጸው፤ ሕያወታቸው ካለፈው ወታደሮች በተጨማሪ 30 ሰዎችን ማቁሰሉን ተናግረዋል።
አክለውም ከፓኪስታን ጋር በድንበር አካባቢ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውለነዋል ነው ያሉት።
ፓኪስታን ይህን አሃዝ በመቃወም 23 የታጠቂ ሀይል አባላት መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ የፓኪስታን ጦር ከ200 በላይ የአፍጋን ተዋጊዎችን መግደሉን አታውቋል፡፡
በዚህም የፓኪስታን ጦር፤ የታሊባን ማኖጅባ ካምፕ ሻለቃ ዋና መሥሪያ ቤትን፣ ጃንዱሳር ፖስትን፣ ቱርክመንዛይ ካምፕን እና ካርቻርን ፎርትን ሙሉ በሙሉ አውድሚያለሁ ብሏል።
የፓኪስታን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞህሲን ናኪቪ የአፍጋኒስታን ጥቃት “ያልተቀሰቀሰ” እና ሲቪሎች የተተኮሱት መሆኑን በመግለጽ፤ የሀገራቸው ጦር "ለእያንዳንዱ ጥቃት" ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቀዋል።
የማዳጋስከር የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ስልጣን እንዲለቁ ተቃውሞ ማስነሳቱ ተገለጸ
በማዳጋስከሩ ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው ከሁለት ሳምንታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን፤ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትም ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አስተዳደራቸዉ በዉሃና በመብራት እጥረት እንዲሁም በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ሕዝባዊ ተቃውሞ በርትቶባቸው ካቤኒያቸውን በማፍረስ አዲስ ካቤኔ እያዋቀሩ ቢሆንም፤ "የሀገሪቱ ችግር የሚፈታው ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ሙሉ በሙሉ ሲለቁ ብቻ ነው" ሲል የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትም ሕዝባዊ ተቃውሞውን በመደገፋ አመፁን ተቀላቅሏል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆኤሊና ፅህፈት ቤት የመንግሥትን ስልጣን በሕገ ወጥ መንገድ ለመንጠቅ ሙከራ እየተደረገ ነው ሲል ክስ አቅርቧል።
ጉዳዩን አስመልክተዉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በህንድ ውቅያኖስ ደሴት ላይ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ በጥልቅ ያሳስበናል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም በሀገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ ሃይሎች ለማዳጋስከር ሰላምና መረጋጋት ሲባል፤ ችግራቸዉን በስክነት እንዲፈቱ ሲሉ መማጸናቸውን አናዶሎ ዘግቧል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ አደባባይ በመውጣት የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማመስገናቸው ተገለጸ
እስራኤላውያኑ አደባባይ የወጡት በሐማስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ታጋቾች ከመለቀቃቸው አስቀድሞ ነው።
አደባባይ ለወጡት እስራኤላውያን ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ታጋቾቹ "ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ" ብለዋል።
ዊትኮፍ አክለውም በጋዛ ተኩስ እንዲቆም እና ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርገው ስምምነት እንዲደረስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማድረጋቸው አመስግነዋቸዋል።
የፍልስጤም ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ የእስራኤል ጦር አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ 500 ሺሕ ነዋሪዎች ወደ ፈራረሰችው ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ሃማስ የሰላም ዕቅዱ አካል የሆነውን የትጥቅ መፍታት አንቀጽ ለመተግበር መስማማቱን የገለጹት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የጋዛ ጦርነት አብቅቷል ሲሉ አውጀዋል፡፡
ትራምፕ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ እስራኤል የገቡ ሲሆን፤ በእስራኤል ፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ተከትሎም ሃማስ የመጀመሪያ ዙር 5 የእስራኤል ታጋቾችን መልቀቁ ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ አንዳለ ግብጽ ጦርነቱን ሊያስቆም ይችላል የተባለውን ስምምነት ከፍጻሜ ለማድረስ ሰኞ ዕለት ጉባዔ እንደምታካሂድ አስታውቃለች።
ትራምፕን ጨምሮ ከ20 በላይ መሪዎች በሻራም ኤል ሼክ የተዘጋጀው ጉባዔ ላይ እንደሚሳተፉ የግብጽ መንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን፣ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ዛሬ ሰኞ በሚጀመረው ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አሐዱ ዓለም አቀፍ መረጃዎች
